እሑድ 13 ጁላይ 2014

ምሥጢረ ሥላሴ

ቅድስት ሥላሴ

• በዚህ ርዕስ ሥር ስለ ቅድስት ሥላሴ (እግዚአብሔር -አ ብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) ሦስትነትና አንድነት
እንማራለን፡፡ ሥላሴን ቅድስት ብለን የምንጠራው ሴት ልጅ ወልዳ እንደምታስገኝ ሥላሴ ዓለማትን ፈጥረው
ስላስገኙ ነው፡፡
• ብዙዎች ስለ ቅድስትሥላሴ ያለውን ትምህርት እየሰሙ በእውነት ክርስቲያኖች በአንድ አ ምላክ ያምናሉ?
የሚያምኑስ ከሆነ አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ምንድር ነው? ብለው ይጠይቃሉ፡፡
• በተዛባ ግንዛቤም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖች ብዙ አማልክትን ያመልካሉ ብለው ይከሳሉ፡፡ የዚህም
ምንጩ“ሥላሴ” የሚለውን ሦስት አማልክት ብለው ማሰባቸው ነው፡፡
• በክርስትና እምነት ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ በክርስትና እምነት በብዙ አማልክት (Polytheism) ማምለክ
የተከለከለ ነው፡፡
• የክርስት ና እምነት ማዕከሉ በአንድ አምላክ ማመን (Monotheism) ነው፡፡
• ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ።እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ
አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ
ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ  ትእዛዝ ይህች ናት።” ማር 12፡29-30፡፡ ብሎ ነግሮናል፡፡
• ብዙዎቻችን ተተንትኖ ከተዘጋጀው ሥነ መለኮታዊ ጥናት ይልቅ ለጊዜያችን በሚመጥን መልኩ ተስተካክሎ
አጠር መጠን ብሎ የቀረበን አ ስተምህሮ እ ንፈልጋለንና በዚህ አጭር ትምህርት የምንማረውም ስለ ሥላሴ
-እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ከገለጠበት አንጻር በመመልከት ነው፡፡
•እግዚአብሔርን የሚመስለው ማንም የለም፡፡እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት “እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።”ኢ ሳ 46፡9 ብሏል፡፡
•እግዚአብሔር በሁሉ ነገር የተለየ የሚተካከለው የሌለ ነው፡፡ “እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?
ይላል ቅዱሱ።”ኢ ሳ 40፡25፡፡
• ዓለምን ሁሉ በውስጣቸው የሚገኘውንም ሁሉ የፈጠረ የሚመስለው የሌለ እግዚአብሔር ነው፡፡ “በመጀመሪያ
እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” ዘፍጥ 1፡1፡፡እርሱንም የሚመስለው የለም፡፡
•እግዚአብሔር ከሰው ችሎታና ግምት የላቀ የመጠቀ ነው፡፡
• የእኛ በሆነው ጠባብ አእምሮ በተዳሰሰ ጥቂት ማብራሪያ እርሱንና መለኮታዊ አምላክነቱን ገልጦ ማስረዳት
አይቻልም፡፡
• የእግዚአብሔር ሀሣቡ፣ መንገዱ፣ ዓላማው (እቅዱ) የሰው ከሆነው የተለየ ነው፡፡ “አሳቤ እንደ አሳባችሁ
መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፦ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እ ንዲሁ መንገዴ
ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።” ኢሳ 55፡8-9 እንዳለ፡፡
• ስለእ ግዚአብሔር የምናውቀው ወይም ያወቅነው የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሁሉንም
ነገር የምናውቅ አይደለንም፡፡
•እግዚአብሔር አማላካችን ስለ ራሱ ያልገለጠልን ምስጢራት አሉ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ “ምሥጢሩ ለአምላካችን
ለእግዚአብሔር ነውየተገለጠውግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለ እኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።”
ዘዳግ 29፡29፡፡
• በዙሪያችን ከሚገኙ ነገሮች ሁሉ የተለየ ከመሆኑ የተነሳ ስለ ርሱ በሰው ቋንቋ መናገርና ማስረዳት ከባድ ነው፡፡
• ስለዚህ መለኮታዊ ነገርን ለማስረዳት ምሳሌዎችን መጠቀም ግድ ይሆናል፡፡ ጌታችንአ ምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በትምህርቱ በርካታ ምሳሌዎችን ተጠቅሞ አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ እንደተናገረው ቢያንስ አንድ ምሳሌ
ሳይጨምር አልተናገረም ነበር፡፡ “ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም። በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም።” ማቴ 13፡34፡፡
•እነዚህ ምሳሌዎች ከሰማእያኑ የዘወትር ሕይወት የመነጩ ናቸው፡፡ ስለ መለኮት የሚነገረውን እውነት የሚመስሉ
ምሳሌዎች ወይም ማስረጃዎች ተሰጥተዋል፡፡ ይህም በግድግዳ ላይ ያለ ሥዕልን እንደ መመልከት ነው፡፡ ሥዕሉ
ተፈጥሮን በቀጥታ የምንመለከትበት ባይሆንም ተፈጥሮን ግን ወክሎ መስሎ ያቀርባል፡፡ የሚወርድ ውሃ በሥዕሉ ላይ
ብንመለከት ለመጠጣት እጃችንን አንዘረጋም፡፡
• ምሳሌ እንደ ሥዕሉ እውነትን ለማስረዳት ይቀርባል፡፡ ምሳሌ እውነቱን ለማስረዳት በጽሁፍም ሊቀርብ ይችላል፡፡ ነገር
ግን እውነቱ አሁንም ከማንኛውም ምሳሌ በላይ ነው፡፡
• “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፡፡” ዮሐ 15፡1-27 በማለት ጌታችን የተናገረው “የእውነተኛ የወይን ግንድ” ምሳሌ
ለቅድስት ሥላሴ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሙሉውን ምዕራፍ ስናነብ ስለ ሦስቱም አካለት ያስተማረውን
ትምህርት እናገኛለን፡፡
• የተለያየ ዓይነት ዛፎች ስለሚገኙበት አንድ የአትክልት ሥፍራ እናስብ፡፡አንዳንዶቹ ሥራቸው ከመሬት ጠልቆ የገቡ
የተፈጥሮ ዛፎች ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ለአካባቢ ወይም ለቤት ማሳመሪያ እንዲሆኑ የተሠሩ ሥር የሌላቸው ሰው
ሠራሽ ዛፎች ናቸው፤ ቀጥሎ የሚገኙት ዛፎች ደግሞ ቅርንጫፎች ቢኖሩአቸውም ሥር ግን የሌላቸው ናቸው፤
በማስከተልም ያሉት ከፕላስቲክ የተሠሩ ዛፎች ሲሆኑ በእነዚህ ሁሉ መካከል ግን እውነተኛ የወይን ዛፍ ይገኛል፡፡
• በዚህ በአእምሮ በታሰበ የአትክልት ሥፍራ እውነተኛውን ዛፍና ጥራቱን እንዴት ለይተን መወቅ እንችላለን?
ወይም እውነተኛውዛፍ ራሱን እንዴት አድርጎ መግለጥ ይችላል? ዛፉ ምንነቱንና ጥራቱን ለይተን ማወቅ
እንዲያስችለን ራሱን የሚገልጥበት መንገድ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡
• ዛፍ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም በዚህ ዓለም የሚገኝ ቁሳዊ ነገር ራሱን የሚገልጥበት መንገድ አለው፡፡ ለምሳሌ
ፀሐይን ብንወስድ መኖርዋን በሚያረጋግጡላት ነገሮች (በክበቧ፣ በብርሃንዋና በሙቀትዋ) አማካኝነት ፀሐይ
ስለመኖርዋ እንናገራለን፡፡ በነዚህም ወሳኝ በሆኑ መገለጫዎቿ አ ማካኝነት ፀሐይ ስለመኖርዋና ስለ ተጽእኖዋ
ግልጽ ታደርጋለች፡፡እ ነዚህ ሦስቱም በሁሉ ዘንድ የምትታወቅ የአንዲት ፀሐይ መገለጫዎች ናቸው፡፡
እነዚህም ሦስቱ የፀሐይ መገለጫዎች ባይኖሩ ፀሐይ ሐሳብ ብቻ የምትሆን ወይም የለችም ተብላ የምትቆጠር
ነበረች፡፡
• እንደዚሁ ስለ እግዚአብሔር መኖርና እንሰማለን እናነባለንም፡፡ ይህ እውነት ግን እግዚአብሔር ራሱን
ባይገልጥ ኖሮ ተራ ሐሳብ ወይም አጠራጣሪ እምነት ይሆን ነበር፡፡
•እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትና የሚገልጥበት የራሱ ብቻ የሆኑ ብቸኛ መንገዶች አሉ፤ ስለ ቅድስት ሥላሴ
የምንለውም እውነት ዋና ምንጭም ይኸው ነው፡፡
• ስለ ሥላሴ በማወቅና በመረዳት እግዚአብሔር አለ እ ንላለን፡፡
•እግዚአብሔር ራሱን ብቸኛ በሖነ መንገድ ገልጧል፡፡

• ስለዚህ ስለ ቅድስት ሥላሴ ከቅዱሳት መጻሕፍት በምናደርገው ፍለጋ የሚከተሉትን እንመለከታለን፡፡ይቆየን
ምንጭ፡-ዘኦረቶዶክስ ድረ ገጽ

ውዳሴ አምላክ ዘሰኑይ

ውዳሴ አምላክ ዘሰኑይ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም አምነን የቂሳርያ ኤጲስ ቆጶስ ባስልዮስ የደረሰውን የልመናና የምልጃ ጸሎት ያለበትን ዘወትር ሊጸልዩት የሚገባ ውዳሴ አምላክ የሚባል መጽሐፍ በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን የአባታችን የባስልዮስ ጸሎት ይጠብቀን ረድኤቱ አይለየን አሜን ይደረግን፡፡
አምላኬ ሆይ ሠውሬ የሠራሁትን ሁሉ ኃጢአት አንተ ታውቀዋለህ ኩላሊትንም ልቡናንም የምትመረምር አንተ ነህ ሠውሬ የሠራሁትን የሥራዬን ክፋት አንተ ታውቀዋለህ ክፉ ሥራዬን አይተህ በኔ ለመፍረድ የማትቸኩል ከተድላዬ የማታዋርደኝ አንተ ነህ በወደቅሁም ጊዜ አካሄዴን የማታዋርድ
አንተ ነህ በጎ አድራጊ ይቅር ባይ ሆይ አትቸኩልም አንተስ መመለሴንም እየጠበቅህ ትዕግስትህን አበዛህልኝ  እኔም ከእንቅልፌ ነቅቼ ይቅርታህን ስፈልግ ወዳንተ ገሠገሥኩ ንስሐ የሚገባውን ሰው ንስሐውን እንድትቀበው አውቄ ባለኝታህ ጸንቼ ወዳንተ ገሠገሥኩ የተናቅሁ ድሀ እኔ እለምንሃለሁ ከወደቅሁበት ታነሣኝ ዘንድ ኃጢአቴንም ትተላለፋት  ዘንድ ንስሐዬንም ትቀበለኝ ዘንድ ከመዓርጌ አዋርዶ ስለጣለኝ ጠላት እንዳይመካ ሳትነፍግ ሳትሳሳ የምትሰጥ በጎ አሳቢ ቸር ጌታችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተ በታመነ ቃላህ በክቡር ወንጌልህ እሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል ብለህ ተናግረሃል (ማቴ ፯፡፯)
አቤቱ ችጋረኛ ድሀ የምሆን እኔም እውነተኛ ነገርህን አለኝታ ተቀብዬ በቃለህ ጸንቼ ኃጢአቴን አምኜ እየማለድሁ እነሆ በፊትህ ቆሜ አለሁ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አለኝታዬን ቆርጠህ እንዳታሳፍረኝ እለምንሃለሁ በደካማነቴ ራርተህ ኃጢአቴን ይቅር ትለኝ ዘንድ ፊትህንም ከኔ እናዳትመልስ ያን ጊዜ አንተን ለመለመን የማልበቃ ኃጥእ በደለኛ እሆናለሁ ያደፍኩ የረከስኩ ነኝና፡፡
ነገር ግን በይቅርታህና በቸርነትህ ብዛት የፍጥረትህን ዕርቅና መዳንን በመውደድህ ነገሬን መልስልኝ ልቅሶዬንም ተቀበለኝ ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ የሥራዬን ክፋት የኃጢአቴን ብዛት አይተህ ዕንባዬን አታሳፍረኝ እንደ እውነተኛ አለኝታህ በክቡር  ስምህ እንደማመኔ ይደረግልኝ እንጂ የነጻች የእጅህ ሥራ የምሆን  እኔ ከባሮችህ ወገን ነኝና እኔም በክቡር ምሳሌህና በመልክህ ተፈጥሬ አለሁና በጥበብህ ከፈጠርኻቸው ከባሮችህ ወገን ስለሆንኩ ስለዚህ ደፍሬ የረከሰች አንደበቴን ገልጨ እለምንሃለሁ፡፡
ኃጢአቴን ይቅር ትለኝ ዘንድ ንስሐዬንም ትቀበለኝ ዘንድ ጽኑዕ ሥልጣን ከሃሊነት ያለህ ቸር ሆይ ጎስቋላ ድሀ የምሆን እኔን በይቅርታህ እንድታድነኝ በቸርነትህ ታደገኝ የበዛች ኃጢአቴንም በደሌንም አርቅልኝ እኔ የተከዝኩ በደለኛ ነኝና፡፡
አቤቱ በምለምንህ ጊዜ ፊትህን ከኔ ከባርያህ አትመልስ አቤቱ ወዳንተ በለመንሁ ጊዜ ይቅርታህን አታርቅብኝ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉሥ ሆይ ወደ አንተ የሚመላለሱትን ዕርቅ ትወዳለህና የሥጋና የነፍስን ደኅንነትንም ትወዳለህና፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የቀናች ሃይማኖትንና እውነተኛ መመነስን ስጠኝ የጸራች ንስሐንም ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሃንሁ፡፡የሚጠሉኝ ጠላቶቼ የክፉ አጋንንት ድንገት በሚመጡበት ጊዜ ወደ አድነኝ ነፍሴ ከሥጋዬ በምትለይበት ጊዜ ወደ አንተ አቅርበኝ እንጂ ካንተ ወደ ሌላ አሳልፈህ አትስጠኝ ሁሉ የሚቻልህ ፈጣሪ ሆይ ጠላቶቼን በኔ አታሠልጥናቸው አታሰናብታቸውም፡፡
ፈጣሪ ጌታ አዛኝ ይቅር ባይ ሆይ የይቅርታና የቅንነት ሣጥን እግዚአብሔር ሆይ ሕይወትን የምትሰጥ በጎ ነገርን የምትወድ አንተ ነህና ስለዚህ ከክፉ ጠላቶቼ አድነኝ እሳቸውን ከመፍራት የተነሣ ነፍሴ ትንቀጠቀጣለችና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ያለክቡር ስምህና ያለ አንተ ለዘላለሙ ድኅነት የለኝም አሜን በእውነት፡፡
መዝሙረ ዳዊት 6

1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።
2 ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ።
3 ነፍሴም እጅግ ታወከች አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው?
4 አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ።
5 በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?
6 በጭንቀቴ ደክሜያለሁ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ።
7 ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ።
8 ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና።
9 እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ።
10 ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።





ቅዳሜ 12 ጁላይ 2014

ውዳሴ አምላክ ዘ እሑድ
የንስሐ ሥርዓት
የመመኘቴ ጸሎት ጌታዬ መድሐኒቴ ኢየሱስ ሆይ እንግዲህ በእኒህ ሁሉ አማላጅነት ወደእኔ ና አትዘግይብኝ ነፍሴ እና ልቤ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጥነህ ና በሉት አፌ ኢየሱስ ክርስቶስን ና በለው  የጻድቅነት ጸሐይ ሆይ የነፍሴን ጨለማ አርቅልኝ ሰማያዊ እሳት ሆይ በዓለማዊ ፍቅር ብርድ ለታሰረብኝ ልቤ ያንተን ፍቅር ሙቀት ስጥልኝ ጌታዬ ሆይ በወንጌል ለመቶ አለቃ ወደ ቤትህ እመጣለሁ ልጅህንም እፈውስልሀለሁ እንዳልከው ለነፍሴ ወዳንቺ እመጣለሁ እፈውስሻለሁ በልልኝ ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ እንዳልናገር አፌን ፈውስኝ ክፉ እንዳለይ አይኔን ፈውስልኝ ክፉ እንዳይሰሩ ነፍሴንና ስጋዬን ፈውስልኝ ጌታዬ ሆይ የእኔን የሎሌህን ክፋት ልትተው ና አትዘግይብኝ ቅዱስ መልአኬ ነፍሴን እጅግ የምትወድ ጠባቂዬ ሆይ ስለ እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይህንን ኑዛዜ በቀኖና በትህትና በሐዘን በፍቅር እንዳደርገው አግዘኝ
ስለኑዛዜ ምክር እንዲህ እያለ የሀዘን ጸሎት እያደረገ በትህትና በልብ ይጸጸት
ዘእሑድ ውዳሴ አምላክ
አቤቱ የጠራ የልቦናን ለቅሶ ስጠኝ ጌታዬ ሆይ በእኔ የጸኑ እሾህ እና አሜኬላን ክዳት ተንኮልንም አጥፋልኝ ዘወትር የሚያቃጥል ልቅሶን ስጠኝ አቤቱ የሰይጣን ገንዘብ የሚሆን የኃጢአትን ጣዕም ስር ከእኔ ነቅሎ የሚጥል ልቅሶን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ከኃጢአት የሚመለሱ ሰዎችን ልቅሶ ስጠኝ አቤቱ የቅዱሳንን ልቅሶ ስጠኝ፡፡ አቤቱ በኃጢአት ሳለ እንዳይሞት ስለራሱ ያለቀሰ የዳዊትን ዕንባ ስጠኝ ፡፡
ጌታዬ ሆይ እንደኔ የበደለ የለምና እኔም እንደወደቅሁት አወዳደቅ የወደቀ የለምና እኔ እንደተፈተንኩት የተፈተነ የለምና፡፡ የሠራኋትም ኃጢአት አንዲት ብቻ አይደለችምና በኃጢአቴ የሌላውን ጽድቅ አጠፋሁ እንጂ፡፡
ጌታዬ ሆይ እኔን ሳላውቅ የፈጠርኸኝ አንተ ነህ ፡፡አንተ ጌታዬ የከበርህ መምህር ኃያል ገናና ነህ እኔ ባርያህ ግን የተናቅሁ ጎስቋላ ደካማ ነኝ አፌ የሚሸት ነው አንደበቴም ዲዳ ነው፡፡ እኔም ኃጥእ ነኝ፡፡ ደካማ ነኝ ልቤም የረከሰ ነው፡፡ በቸርነትህ ተጠግቼ እጠራሀለሁ የጻድቁንና የኃጥኡን ጸሎት የክፉውን የምትሰማ አንተ ነህና ያለ አንተም ቸር የለምና እንደ አንተ ያለ ይቅር ባይ የለምና፡፡ 
ጌታዬ ሆይ የነጻች የእጅህ ሥራ ነኝና ስለ ኃጢአቴ ቸል አትበለገኝ አቤቱ ሥጋዬን አንጻው ሕፀፄን አውቄ ከመጠኔ እንዳልወጣ አቤቱ ጠላት ድል እንዳይነሳኝ ኃይልን ስጠኝ በክብርት ጥምቀትህ የተሠራች ቤት ሥጋዬን እንዳያፈርሳት በከፋች ኃጢአት እንዳያሳድፋኝ ስለ ኃጢአቴ ሥርየት ወደ አንተ እማፀናለሁ፡፡ አቤቱ ነፍሴ እንዳትጎዳ አደራህን ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለ ጉስቊልናዬና ስለ ጉዳቴ እማፀናለሁ ስለ ኃዘኔና ስለ መከራዬ በአንተ እማፀናለሁ ስለ መልኬ ጥፋትና ስለበደሌም በአንተ እማፀናለሁ፡፡ ብሩህ ሁኜ ሁሉን እንዳላይ የጠቆርሁ ኃጥእ ነኝና ላልተመለሱ ፍርድህንና ሞትን ማሰብ ስጠኝ አቤቱ በደሌንና ነውሬን የሚያጥብ ዕንባን ስጠኝ አቤቱ፡፡አቤቱ አንተን የሚያገለግል ዕንባን ስጠኝ አቤቱ ልዩ እንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ቀጡ ዕንባን ስጠኝ፡፡አቤቱ ኀዘኔን የሚያርቅልኝንና የፊቴን ጥቁረት የሚያርቅልኝ እንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ከዓይኔ ፈሶ የአካሌን እድፍ የሚያጥብልኝ ዕንባን ስጠኝ፡፡  አቤቱ አንተን ደስ የሚያሰኝ ደስ ብሎህ የምትቀበለው ዕንባን ስጠኝ፡፡
የተነሳሕያንን ዕንባን የምትቀበል ሆይ ወንድማቸውን ከመቃብር እስክታነሣላቸው ድረስ ሳያቋርጡ እንዳፈሰሱት እንደ አልአዛር እህቶች ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡አንተ የተቀበልከው ጽኑ ልቅሶን እንደ አለቀሰ እንደ ጴጥሮስ ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡
ከንጹሐን እግሮችህ ላይ ዕንባዋን አፍስሳ በራሷ ፀጉር  እንደ አደፈችው እንደ ሴሰኛዪቱ ሴት ያለ ልቅሶን ስጠኝ፡፡ልቅሶዋም ስለ ንስሐዋና ስለ ሕይወትዋ ሆነ፡፡
ልጅዋን እንዳነሣህላት እንደ ጎስቋላይቱ ድኻ ልቅሶ ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡አልጋዬን በዕንባዬ አርሰዋለሁ ምንጣፌን በዕንባዬ አጥበዋለሁ ብሎ በስድስተኛው መዝሙር  እንደ ተናገራት እንደ ዳዊት ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡
አቤቱ እንደ አባቶቼ መምህራን ያለ ዕንባን ስጠኝ፡፡ እንደ ተነሳሕያን ኃጥአን ያለ ዕንባን ስጠኝ አቤቱ እንደ ባሕር በምትፈስ ዕንባ እጠበኝ፡፡ አቤቱ ጌታ ሆይ የተዘጋ ደጅህን ክፈትልኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ የማያቋርጥ የዕንባን ምንጭ ክፈትልኝ፡፡ አቤቱ የማያቋርጡ የዕንባዎች ጎርፍን አፍስልኝ ፡፡ስለበደሌና ስለኃጢአቴ ብዛት ስለ ነፍሴም ጉዳት የንግድ ገንዘብ ስለሚሆን ስለራሴም ጥፋት አቤቱ ይቅር በለኝ፡፡
ጌታዬ ሆይ ነፍሴን ከሥጋዬ እስክትለይ ርዳት የተበላሸች የወይን ቦታ ስለ መልካም ፍሬ ፈንታም ርኩስ ፈቃዴና ኃጢአቴ የሰለጠኑበትን አርማት ኮትኩታት፡፡
ጌታዬ ሆይ ወደ መመቸቴ ፈቃድ አታግባኝ፡፡ ፍርድህንም ፈርቼ ነፍሴን ከፊትህ ጥያታለሁ፡፡ አቤቱ ከይቅርታህ ለምመጸወት ድኻ እዘንልኝ ከርኅራኄህ ትሩፋት የምለምን ችግረኛህንም አታሳፍረኝ፡፡ በበደሌና በኃጢአቴ መታደስ  እኔ ወራዳ ድኻ ነኝና በከሃኒነትህ ከኃጢአት እድፍ አንጻኝ ስምህን ለሚወዱ ለባሮችህ ባዘጋጀኸው በንስሐ ዕንባ እጠበኝ ፡፡
አቤቱ ኃፍረቴንና ኃሣሬን ሠውራት፡፡ በፍጥረቱ በምትፈርድበት ጊዜ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ስማኝ ፈጣሪዬ ሆይ ፊትህን ከልመናዬ አትመልስ፡፡ልቅሶዬን ተቀበል ዕንባዬንም አታሳፍር አኔ ጥገኛህ ነኝና ጌታዬ ሆይ ስለ ኃ ጢአቴ ብዛት እገዛልኻለሁ፡፡
ጌታዬ ሆይ እስከዘመኔ ፍጻሜ ከቡር ስምህን አመሰግናለሁ ኪሩቤል ሱራፌልም የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ አንተን ያመሰግናሉ ለዘላለሙ አሜን በእውነት ይደረግልገኝ፡፡

መዝሙረ ዳዊት 120
1 ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?
2 ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
3 እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም የሚጠብቅህም አይተኛም።
4 እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።
5 እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።
6 ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።
7 እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።
8 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።
ክርስትናና ወጣትነት/ክፍል አንድ/
በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን
  ሰላሌ ሃገረ ስብከት እያለሁ ነዉ።አስታውሳለሁ።ወረዳ ላይ ለአገልግሎት ስወጣ የሚያጥመኝ የሚገርምኝም ነገር ነበር።የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ሳስተምር ከመካከላቸው ሁል ጊዜ አንድ አዛውንት አያለሁ።ወጣ ካለ ቦታ ከገጠር ነው የሚመጡት። ብርቱ የሆነ መንፈሳዊ ስሜት አላቸው።በአካባቢያቸው ብዙ ጨሌ አቃጥለዋል።በዛ ያሉ ምዕመናንም ለንሰሓ አብቅተዋል።ለገጠሩ ሕብረተሰብ ጥሩ አርበኛ ናቸው።እኒህ አረጋዊ ጉባኤ ሲያበቃ ይጠራቀሙትን አንድ መድበል ጥያቄ ይዘው ይመጣሉ።ከዚያ በቃ መጽሓፍ ቅዱስ እየገለጡ መጠየቅ ነው።መናፍቃንን አጥብቀው ስለሚቃወሙ ለእነርሱ የሚሆን መልስ በጉንጫቸው አለ።                
           ታድያ ብዙ ጊዜ የሚናገሩት ነገር ነበር።እንደው እድሜን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም እንጂ ምነው በተቻለና በመለስኩት፣  በእኛ ጊዜ የሃይማኖት ትምህርት እንዲህ ስላልተስፋፋ ባተሌ ሆነን ነው የኖርነው ይላሉ። እናንተ ታድላችኋል ዕድሜያችሁን እየተጠቀማችሁበት ነው በማለት በቁጭት ይናገራሉ። መዝሙር ሲዘመር ፣ ስብከት ሲሰበክ፣ ሰንበት ት/ቤት ድራማ ሲሰራ በቃ እርሳቸው ከራሳቸው ጋር ይሟገታሉ። እድሜ ከንቱ ሳላውቀው ሄደና በቃ ወጣትነቴ አመለጠኝ ማለት የዘወትር ተግባራቸው ነው።
            አንድ ቀን መከርኳቸው መንፈሳዊ ቅናት መቅናታቸው መልካም ቢሆንም ለቀቢፀ ተስፋ እንዳይዳርጋቸው ይተዉ። የእርስዎ የጥሪ ዕድሜ ይሄ ከሆነ ስልሳኛ አመትዎንም እንደ ሃያና ሰላሳ ይቆጥርልዎታል ይልቅስ ባልዎት ዕድሜ እየተጠቀሙ ይበርቱ ብዪ አጽናናኋቸው ።በወጣቱ እንቅስቃሴ የሚገረሙ ምዕመናን ይህን ይላሉ ።ምነዉ ዳግመኛ በተፈጠርኩ ፣ምነው ወጣትነቴን በድጋሚ ባገኘሁት ይላሉ።ግን አይሆንም ዕድሜ ከነጎደ ነጎደ ነው።ከመፀፀት አንዷን ዲናር /መንግሥተ ሰማያትን/ ዋጋቸው ሆና ለመቀበል በገቡበት ሰአት ገብተው ታማኝ ሆነው ድራሻቸውን ቢወጡ መልካም ነው።የሦስተኛውም ፣ የስድስተኛውም ፣ የዘጠነኛውም ፣ሰአት ዋጋ አንድ ዲናር ነው።
            ዕድሜ ሳይሰሩበት ያለፈባቸው እንዲህ እንዲጽናኑ እየመከርን ወጣትነት በእጃችን ያለ ግን ብዙ ይጠበቅብናል።ዛሬን እንደ ቀልድ ባተሌ ሆነን ካሳለፍነው ነገ መጸጸት እንድሚመጣ መዘንጋት የለብንም። ወጣትነታችን ጥሎን ሳይሄድ እያንዳንዱን ደቂቃ ሰከንድ እንዳይባክን አድርገን ማሳለፍ ይጠበቅብናል።ዕድሜ በላያችን ሳይሮጥ እኛ በእድሜ እንሩጥ።ጊዜን እየገደልነው ሳይሆን እየተጠቀምንበት እንዲያልፍ እናድርግ።ለሌላው ንብረታችን ከምንሳሳው በላይ ለዕድሜ እንሳሳ።መክሊቱን ቀብሮ ያለ ትርፍ እንደተገኘው ሰነፍ ባሪያ የተሰጠንን ጊዜ ሳናተርፍበት ባለቤቱ እንዳይመጣብን እንጠንቀቅ።
            ለመጸለይ ዓይኔን ፣ለመስገድ ወገቤን ፣ለመፆም አቅሜን የማንልበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።ከልብ ከተነሳን በዚህ ዕድሜ በፈጣሪ እርዳታ ብዙ መስራት እንችላለን።ለአገልግሎት ከአንዱ ስፍራ ወደ አንዱ ብንሮጥ፣ገዳማቱን በየሥፍራው ዞረን ብንሳለም ፣አበውን ለመርዳት ገንዘብ ብናወጣ ፣ብንረዳ ፣መንፈሳዊ ማህበር ብንመሰርት ሁሉም ይቻላል።ጉልበትን ። ገንዘብን፣እውቀትን፣ሁሉንም በስራ ለማዋል የሚመቸው በዚህ ዕድሜ ነው።
           የመናፍቃንን ተንኮል ለመከላከል ዘመኑን ዋጅተን መልስ ማዘጋጀት የምንችልበት እድሜ ወጣትነት ነው።በየዋህነት የኮበለለውን  ምዕመን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ በአፍ በመጽሐፍ የምንልበት ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ ሌትና ቀን የምንደክምበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።በዚህ ዕድሜ ቅዱስ ዮሐንስ ነገረ መለኮትን አርቅቆ አምጥቆ እንደጻፈ / ዮሐ 21-24 /አትናቴዎስ የሃይማኖት ጸሎትን ከሦስት መቶ አስራ ስምንት ሊቃውንት ጋር በመሆን እንዳረቀቀ አንርሳ።
           ሰማዕትነት ቢመጣ አንገትን ለሰይፍ ለስለት ፣ሰውነትን ለሞት ለመስጠት የሚታገሱበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።ስለቤተክርስቲያን ሕይወትን እንኳን ዋጋ አድርጎ ለመስጠት ይህ ዕድሜ ይመቻል።ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የአይሁድን ቁጣ ሳይፈራ እውነትን መስክሮ በሰማዕትነት ያረፈው በእዚህ እድሜ መሆኑንም አንዘንጋው።ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዐላውያን ነገሥታት ፊት ስለአምላኩ መስክሮ የገጠመውን መከራ ሁሉ በጽናት የተቀበለው ገና በሃያ ሦስት ዓመቱ ነው።ከቅዱሳት አንስት ቅድስት አርሴማን የመሳሰሉ እናቶች መከራን ስለ ሃይማኖታቸው የተቀበሉት በዚህ እድሜ ነው።
           ከዚህ ሁሉ አንጻር በወጣትነት የዕድሜ ክልል ያለን ቤተ ክርስቲያንን በጽናት በትጋት ማገልገል ይጠበቅብናል።ዕድሜያችን ለመንፈሳዊነት የሚመች እንደመሆኑ እንጠቀምበት።በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችንን ማሰብ እንዳለብን አንዘንጋ።/መጽ መክ 12-1/ ውድ የሆነዉን የዕድሜ ክልላችንን ለእግዚአብሔር አንንፈገው።ይልቁንም ከእጁ የተቀበልነዉን እድሜ ፣ጤና ….መልሰን ለፈጣሪ እንስጠው።ጤናችን ፣ጉልበታችን ፣ገንዘባችን ሁሉ የእርሱ ነው።የእኛ የሆነ አንዳች ነገር የለንም።ሌላው ቀርቶ እኛም እራሳችን የእርሱ ነን።ይህንን ሳንረሳ ሁል ጊዜ ለፈጣሪ ታማኝ እንሁን።
          ወደፊት በዚህ ዓምድ ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን እንዴት መመላለስ እንዳለበት ፣መንፈሳዊ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለበት በሰፊው እንመለከታለን ።የሚገጥሙትንም ፈተናዎች በጊዜዉና በሰዓቱ እንዳስሳለን።ለአሁኑ ይቆየን።