ስለ ቤተ ክርስቲያን /አቅሌስያ/
በእግዚአብሔር ፈቃድና ስምረት ከዓለም ሁሉ የተመረጠች የተሰበሰበች የአህዛብና የአይሁድ ቅሬታ ምንስ ልዩ ልዩ አባላቶች
ቢኖሩባት በአንድ በክርስቶስ ሥጋ አንድ አካል የሆነች አንድ ፍጹም ምሉዕ አቅመ አካል ለመሆንም እስክትበቃ ድረስ በእግዚአብሔር
ቃል ወደ ራስዋ ወደ ክርስቶስ የምታድግ ክርስቶስም የማዕዘኑ ራስ ሲሆን በነቢያትና ሐዋርያት መሠረት ላይ ምዕመናንዋ መንፈሳውያን
ድንጋዮች ሆነው ለአንድ ቅዱስ ቤተ መቅደስነት የሚሠሩባት እግዚአብሔርም አስቀድሞ በልጁ መልክ ምሳሌ እንድትሆን ባቀደበት ገንዘብ
በቃሉና በደሙ ታጥባ ቅድስትና ንጽሕት ሆና በመንፈስ ሙሽራነት በክርስቶስ ቀኝ ለመቀመጥ የተመረጠች የእስራኤል ዘነፍስ ማኅበር መንፈሳዊት
ጽዮን የምትሆን አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳለች እናምናለን፡፡
ምንም እንኳን በሜዳዊ ሥርዓቶችዋ ምክንያት ገብተው በመቀላቀል መስለዋት የአፍ ክርስቲያኖች ወገኖች ቢታዩባት እግዚአብሔር አባላቶችዋን
በሚያውቅበት ምስጢር የማትታይ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር በመንፈስ
በመያያዝዋ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ስለ ሆነች በጋለና በተቃጠለ ፍቅር በውስጥዋ ያለውን የክርስቶስን ወንጌሉን ብርሃን በቃልና በአካሄድ
በልብም ንብረት እየገለጸች ይህንን ዓለም የምታስተምር ቅድስት ናት ስንል እናምናለን፡፡
ቤተ ክርስቲያንም ስንል ኀሳቡን በእዚህ ላይ እንደተመለከትነው ስለ ትልቅና ስለ ትንሽ ሕንጻ ሳይሆን ስለ ምዕመናን አንድነት
መናገራችን እንደሆነ ከኒቅያና ከሐዋርያት ሥርዓተ ሃይማኖት ጠቅሰን በሚከተለው እናስረዳለን፡፡
ወነአምን በአሐቲ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርይት ፡፡
የሐዋ 2፡47
በሁሉ ዘንድ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን
እንዲሁም ሳዊሮስ ፡-
በሐዋርያት ስብከት አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ሁሉ ሐዋርያዊት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ይሆናሉ፡፡እርስዋ ከአሕዛብ
ሁሉ የተሰበሰበች በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰች የቅዱሳን ሐዋርያት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡ ብሎ አስረድቶ ተናግርዋል