የቅዱስ መልአክ ጸሎት
የምትጠብቀኝ መልአክ ሆይ ዛሬ ወደ ቅዱስ ቁርባን
የምቀርብ ነኝና ቁርባንም ስለ ክብሩ ብዛት የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ ሥራት ነውና እጅግ እፋራዋለሁ ስለዚህ አንተ ተከተለኝ ጌታዬ
የሚገባ ልመና እንድለምነው አንተ ጌታዬን እንዴት እቀበልሃለሁ ይሆን እንዳልል ለልቤ መንፈሳዊ እውቀትን አሳይልኝ፡፡የኔ ልብ ካንተ
በዚህ ታቦት ዙርያ ከሚቆሙት ከባልንጀሮችህ ልብ ጋራ እንዲሆን የልብ ትሕትና የልብ ፍቅር አስተምረኝ፡፡የምትረዱ ቅዱሳን ሁሉ ተከተሉኝ
ጠብቁኝ፡፡
ዘቀዳም
ውዳሴ አምላክ
በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አምናለሁ፡፡መግደልና
ማዳን በሚቻለው አመንሁ ሞትና ሕይወት በእጁ ባለ አመንሁ መንፈሳዊውንም ሕይወት በሚሰጠው አምናለሁ፡፡በኪሩቤል ላይ በተቀመጠው አምናለሁ፡፡ምድርን
ባያት ጊዜ እስከ መሠረቷ እንድትንቀጠቀጥ በሚያደርጋት አምናለሁ፡፡
አዳምን ልጆቹንም በምሳሌው በፈጠራቸው አምናለሁ፡፡አዳምና
ልጆቹንም ለማዳን በመምጣቱ አምናለሁ ከንጽሕት ድንግል ከእመቤታችን ሰው በመሆኑ አምናለሁ፡፡ እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ ባለው አምናለሁ፡፡
የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ በኔ ያመነ አይሞትም
ቢሞትም እኔ አሥነሳዋለሁ ባለው አምናለሁ ለፍጥረቱ ሕይወትን በሰጠ አምናለሁ እኔ በአብ እኖራለሁ አብም በኔ ይኖራል ‹‹እኔና አብ
አንድ ነን›› ባለው አምናለሁ ኃጥአንን ወደ ንስሓ ይጠራ ዘንድ በመጣው ለፍጥረቱም ኃይልና ሥርየትን በሰጠው አምናለሁ፡፡
በጽሩይ ልቡና የሚለምኑትን በርኅራኄው ብዛት በሚቀበላቸው
አምናለሁ፡፡ሳይሣሣ በሚሰጥ አምናለሁ ሥጋ ያለውን ሁሉ ልመና ሰምቶ ተስፋ በማያስቆርጥ አምናለሁ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለኝ ፡፡
ይቅር ትለኝ ዘንድ ይቅርታህን አያለሁና ያለ አንተ ይቅር ባይ ባይኖር ጌታዬ ሆይ የቀኝ እጅህ ፍጥረት ነኝና ይቅር በለኝ በደለኛ
ኃጥእ የነበርሁ እኔ ላገለግልህ መጥቻለሁና ይቅርታህና ርኅራኄህ የበዛ ፈጣሪ ይቅር በለኝ ፡፡ በፊትህ የበደልሁ እኔ በፊትህ ወድቄ
አለሁና በጎነትህ የሰፋ ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ የተጠመቁ ክርስቲያንንም ሁሉ ይቅር በላቸው፡፡
ጌታዬ ሆይ በርኅራኄህ ብዛት ይቅር በለኝ፡፡ጌታዬ
ሆይ በቸርነትህም ብዛት ይቅር በለኝ፡፡
ለኃጢአቴ ሥርየት ስለ ሠራህልኝ ጥምቀቴ ይቅር በለኝ፡፡ ኃጢአታችን ሊሠረይበት እንበላው ዘንድ ስለ ሰጠኸን ስለ አምላካዊ ሥጋህ ይቅር በለኝ፡፡የዘላለም
መድኃኒትና ይቅርታን ስለ ሰጠህባት ስለ ሐዲሲቱ ሕግ አቤቱ እኔን ባርያህን ይቅር በለኝ፡፡
ጌታዬ ሆይ ወደ ተወደደ ልጅዋ ይሰማል እንጂ ልመናዋ
በማይነቀፍ ይቅር ባይ አማላጅ በምትሆን በእመቤታችን በአማላጃችን ይቅር በለኝ አቤቱ ጌታዬ ሆይ ስለ ኃጢአቴ ብዛት ይህን ካንተ
ከመቀበል ምንም የበቃሁ ባልሆን ይቅር በለኝ፡፡የኃጢአቴንም ብዛት አትይ ያለ ንስሓ ኃጢአት የሚያስተሠርይ የለምና፡፡
የኃጢአቴን እድፍ ከይቅርታህ ብዛት ጋራ የምታጽብ
አንተ ስለሆንክ፡፡ለጋስ ሆይ ቸር ሆይ ይቅር በለኝ፡፡ሰማይ ስንኳ በአንተ ዘንድ ንጹህ አይደለምና የመላእክት ጭፍሮችም በአንተ ዘንድ
ንጹሐን አይደሉም፡፡ንጹሐን ባይሆኑ ከእርሳቸው ወገን ከመዓርጋቸው የተዋረዱ አሉና ስለዚህ የፍጥረት ጌታ ሆይ በአንተ ዘንድ ንጹሕ
የለምና ይቅር በለኝ እላለሁ፡፡
ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ ወራቴ በከንቱ አልቋልና
ዘመኔም በከንቱ ተፈጽሟልና ወደ ሌላም ዘመን እንድመለስ ተስፋ የለኝም፡፡
ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ ፡፡በዕዳ ተይዤ አለሁና
ነፍሴን ከኃጢአት ማሰሪያ የማስፈታበት የበጎ ሥራ ገንዘብ የለኝምና ክፉ ሥራዬም በዝቷልና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡
እነሆ መከር ደርሷልና አጫጆችም ከራስጌዬ ቁመዋልና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡የወይን
መቁረጫው ጊዜው ደርሷልና ወይኑ ግን ጮርቃ ነው አይረባኝምና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡እነሆ በማያፈራው ዕንጨት
ሁሉ ምሳር ተቃጥቷል ክፉ ዕንጨት የተባለም አንተን የማገለግልበት በጎ ሥራ የሌለኝ እኔ ነኝና ጌታዬ ሆይ
ይቅር በለኝ፡፡
እኔ ቸል ስል ሞት ደርሶብኛልና ጌታዬ ሆይ እዘንልኝ፡፡ለመንገዴ
ስንቅ የለኝምና መንገዴም እጅግ የምታደክም ናትና ምክንያትም ምላሽም የለኝም ጌታዬ ሆይ ራራልኝ፡፡መልእክተኛ ወደኔ በመጣ ጊዜ እንዳያስቸኩለኝ
ከዚህ ዓለም ለመሄድ የበቃሁ አይደለሁምና በሞት ስጨነቅ መንገድም የሚገኘኝን
አላውቅምና ጌታዬ ሆዬ እኔን ግን ያንተን ረዳትነት ተስፋ አደርጋለሁ ያለ ይቅርታህም ተስፋ የለኝም ጌታዬ ሆይ ከርኅራኄህ
አታሳፍረኝ በድሎ ወደ አንተ በንስሐ የተመለሰውን አታሳፍረውምና ከመሓሪነትህና ከስጦታህ አታሳፍረኝ ከበዛች ለጋሥነትህም፡፡
ጌታዬ ሆይ ከመመካት አድነኝ ከኩራት አድነኝ ከትዕቢት
አድነኝ ልቡናን ከማሳደግ ራስንም ከፍ ከፍ ከማድረግ ከቅናትና ከቂም ከሐሜትም ከባልንጀራም መፍረድ አድነኝ፡፡
አቤቱ ጌታዬ ሆይ ከታናሹም ከታላቁም ኃጢአት ሰይጣን ከሚያሰራውም ሥራ ሁሉ አድነኝ፡፡ሥጋንም ደስ ከማሰኘት አድነኝ ፡፡ከጉዳትም አድነን፡፡
አቤቱ ከዳተኛ ወንጀለኛ ከሚሆን አምላካዊ ፍቅርንም ከሚጠላ ከባላጋራዬ ከዲያቢሎስ እጅ አድነኝ፡፡ጠላቴንም በእኔ አታሰናብተው ድል
መንሣትንም አትስጠው ድል በነሣ ጊዜ በእርሱ ኃይል ድል እንደነሳኝ አድርጎ እንዳመካ ጌታዬ ሆይ በመዓልት በሌሊትም በጊዜው በየሰዓቱም
ሁሉ ጠብቀኝ ከክፉም ከርኩስም ሕሊና ለሚያዋርዱና እንደ እሳት ከሚያቃጥሉም ተጠብቄ እንድኖር አድርገህ ትእግሥትን ስጠኝ በቦታዬም
እንድኖር አድርገኝ ሌባ እንዳይሰርቀኝ ከቦታዬም እንዳያናውጠኝ ገንዘቡ ጠፍቶበት ከወንድሞቹ እንደተለየ እንደ ባዕድ እንዳያደርገኝ
በጠላቶቼ ፊት አትግለጠኝ እንዳይስቁብኝና እንዳይዘባበቱብኝ የተሠወረ ኃጢአቴንም እንዳይገልጹብኝ በቦታዬ አጽናኝ እንጂ መልካም ፍሬንም
እንደምታፈራ እንደ ሠሌን ሥር ጽናት በልቡና ጽናትና በነፍስ ዝምታ በቦታዬ ትከለኝ፡፡
አቤቱ ጌታዬ ሆይ የነፍሴን ነገር እያሰብኩ በኃጢአቴ
አለቅስ ዘንድ ልቡናዬ እንዳይታወክ ነፍሴንም በመውጣት በመግባት ካንዱ ወደ አንዱ መዞርን እንዳታደርግ ይህም የሰይጣን ጦርነት ነው
ዘመኔም በሥራ ፈትነትና በዙረት እንዳይፈጸም የዲያብሎስንም ኃይል ከሃሊነት ባለው ሥልጣንህ አጥፋው እኔ ባርያህ በሥራዬ ሁሉ ደካማ
ነኝና አባትና እናት እንደሌሉት ሕፃን በየጊዜው ሁሉ ወደ አንተ አንጋጥጣለሁ ባል እንደሌላት እንደተዋረደችም ሴት ደዌውም እንደ
ጸናችበት ድውይ በቁስል ላይ ቁስል እንደ ተጨመረበት የሚፈውሰውንም ባለመድኃኒት እንደሚሻ፡፡
መዝሙረ ዳዊት 85
|
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ