ቅዳሜ 19 ጁላይ 2014

ክርስትናና ወጣትነት/ክፍል አራት/


 ካለፈው የቀጠለ /ዓላማበ ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን                    
 ወረት      
አንዳንድ ወጣት ብዙ ነገሮችን መሞከር ደስ የሚለው አለ:: በዓለማዊ ሕይወቱ አንድ ሰሞን ስፖርተኛ ሌላ ሰሞን ደራሲ ሌላ ሰሞን የኮሌጅ ተማሪ ሌላ ወቅት ደግሞ ዳንሰኛ ወዘተ...   ይሆናል::ጠዋት ተነስቶ ሲሮጥ ያዩት ሰዎች ስፖርተኛ ሆነ ብለው ተናግረው ሳይፈጽሙ ሐሳቡን ቀይሮ ደራሲ ለመሆን ፀጉሩን ሲያሳድግ ያገኙታል::ሁለትና ሦስት አንቀጽ የጻፈውን ጽሑፍ  እያሳያቸው አጀማመሬ እንዴት ነው ? ጥሩ ደራሲ ነኝ ሲል ያዳምጡታል።በደራሲነቱ ጥቂት ወራት እንደሰነበተ የተማረ ለመሆን ኮሌጅ ገብቶ ደብተር ጨብጦ አሁን በቃ ቆርጫለሁ ተምሬ ሃገሬን ለማገልገል አስቤአለሁ ይህች ሃገረ የተማረ የሰው ሃይል እጥረት አለባት ማለት ይጀምራል። ብዙም ሳይቆይ ሀገሪቱ የምታድገው በትምህርት ሳይሆን በኢንቨስትመንት ነው በሚል ነጋዴ ለመሆን የአስመጪና ላኪ ፈቃድም ያወጣል።

እንዲህ ዓይነት ወረተኛ ሰው በሃይማኖትም ሁሉን ልሞክር ቢል አይደንቅም። አንድ ሰሞን ፕሮቴስታንት ሆኖ  የሰፈሩን ሰው ሁሉ ካልሰበኩ ፣ ሌላ ሰሞን የጄሆቫ እምነት ተከታይ ሆኖ ኮትና ሱሪ ለብሼ ካልዞርኩ፣ ትንሽ ሲቆይ ደግሞ ሰልሜያለሁ በሚል ጀለቢያ ለብሼ ሶላት ካልሰገድኩ ሊል ይችላል። ይህንን ሁሉ  ሲሞክር ሰንብቶ አሁን ወደ እናት አባቴ ሃይማኖት ተመልሼያለሁ ጥሩ ኦርቶዶክስ እሆናለሁ በሚል ወደ ቤተክርስቲያንም ለመጣ ይችላል ።ቤተክርስቲያን ሲመጣ ነጠላ አጣፍቶ በጠዋት ለቅዳሴ ይገሰግሳል።እንደልማዱ ወረቱ እስኪያበቃ  ይህንንም አይቼዋለሁ ለማለት ጥቂት ጊዜ ትጉህ ይሆናል።እንዲህ ያለ ሰው የእግዚአብሔር ቸርነት ተጨምሮ ጥሩ ጓደኛ አጋጥሞት ወደ ልቡ ካልተመለሰ ወረቱ ሲያበቃ በመጣበት እግሩ ተመልሶ መሄዱ አይቀርም።ከዚህ አንጻር ወረተኛ የሆኑ ወጣቶችን  ፍጥነታቸውን ገትተው በተረጋጋ መንፈስ እንዲጓዙ መምከር የክርስትና ፍጻሜው ሩቅ እንደሆነ ማሳወቅ ተገቢ ነው።

እስኪ እራስህን መርምር ክርስትናህ  ወረታዊ ነው  ወይስ  ገብቶህ እየፈጸምከው ትገኛለህ።ከአጀማመርህ  አንስቶ እስከአሁን ያለህን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለመገምገም ሞክር።ተለዋዋጭ ነው ወይስ ቀጥተኛ?የጸሎት ሕይወትህ ፣ለአገልገሎት ያለህ ትጋት እንዴት  ነው።ዛሬም  እንደጥንቱ ነው ወይስ ተዳክመሀል ?እየተለዋወጠ ያለ ነገር ካለ  ወረት እያጠቃህ መሆኑን አትርሳ።መጠኑ ይለያይ እንጂ  የወረት ክርስትና  በብዙዎች ዘንድ አለ።ይህን አስብና  ከወረት ራቅ።የቀደመ ፍቅርህ ወዴት አለ?እንዳትባል  ከወዲሁ አስብበት/ራእ ዩሐ 2-4/።ክርስትና እስከመቃብር መታመን መሆኑን አትርሳ።ሳትባረድ  እስከመቃብር ለመታመን ወደፈጣሪህ  ጸልይ።ሁልጊዜም እንደጀማሪ ክርስቲያን  በፍሪሃ እግዚአብሔር ፣ በትጋት አገልገል።ይህን ካደረግህ የክርስትና ጉዞ ዓላማ ገብቶሃል ማለት ነው።
  ችግር
ችግሮች ገፍተውት ፣ ከችግሩ ለመላቀቅ ወደቤተ ከርስቲያን የሚመጣ ፣መንፈሳዊ የሚሆንም አለ።ለምሳሌ ትምህርቱን ጨርሶ ሥራ ያጣ ወጣት ሥራ እስኪያገኝ ከቤተሰብ ጥገኝነት ነፃ እስኪወጣ  ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ ይችላል። እንዲህ ያለ ወጣት ችግሩ እስኪፈታለት ማንኛውንም መንፈሳዊ ተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም።በዓውደ ምህረት ፣በሰንበት ትምህርት ቤት ትጉህ ተማሪ ይሆናል።መዝሙር ይዘምራል፣ያስቀድሳል፣ ኪዳን ያደርሳል፣ ሁሉንም በትጋት ያከናውናል። ንስሐ ግባ ቁረብ ቢባል እንኳን ወደ ኋላ አይልም።በዚህ መልኩ  ይቆይና ችግሮቹ ተፈትተው ሥራ ሲያገኝ ጫን ያለ ገቢም ባይሆን ራሱን የሚያስተዳድርበት ገንዘብ መቁጠር ሲጀምር ዓለም ለምኔ እንዳላለ ክርስትና ለምኔ ማለት ይጀምራል።
   እንዲህ ያለው ሰው ክርስትናን የሚሸሸው በመንቀፍ አይደለም። ሰዎች ግምት ውስጥ እንዳያስገቡት በፊት ለፊት ነቀፋም ትችትም የለም።ነገር ግን ራሱን በሥራ ወጣጥሮ ሩጫ እንደሚበዛበት ጊዜ እንደሌለው መናገር ይጀምራል። እሁድ ቀን እንኳን ለቅዳሴ ጊዜ አላገኘሁምና ይቅርታ ይላል። በእርግጥ ሥራ ሲጀምር እንደቀድሞ ላይሆንለት  ጊዜ ይጣበብበት ይሆናል። ነገር ግን ከአንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድምና ለቤተክርስቲያን ጥቂት ጊዜ አይጠፋም። ችግሩ ያለው ባለቤቱ ላይ ነው።ጊዜው ላይ አይደለም። ይህ ወጣት  የምፈልገው ጉዳይ ተስተካክሎልኛል ብሎ ስለሚያስብ ከጓደኞቹ ጋር ይዝናና ይሆናል እንጂ በትርፍ ጊዜው ቤተክርስቲያን አይመጣም።የሚገርመው እንዲህ ያለ ወጣት ከቤተክርስቲያን እንዳይጠፋ ሥራ መጥፋት፣ ችግር መምጣት ያለበት ይመስላል።  

 
ችግር ሲባል ሥራ ማጣት ብቻ አይደለም ።መታመም አንዱ ነው።የታመሙ ወጣቶች  ተስፋ ቆርጠው በመዳንና በመሞት መካከል ሆነው ወደ መንፈሳዊነት ቢመጡ ለጊዜው ፍጹማን ሆነው ይታዩ ይሆናል ።በጠበል ሥፍራ በገዳማት በታላላቅ በዓላት ላይ ነጠላ አጣፍተው እያሸበሸቡ እየዘመሩ ይታያሉ፡፤ ግሸን፣ ላሊበላ፣ ዝቋላ፣ ደብረ ሊባኖስ ዋልድባ፣ እነዚህንና ሌሎች ታላላቅ ገዳምትን ሁሉ ያዳርሳሉ።እግዚአብሔር ከጭንቀታቸው እስኪገላግላቸው ጠንክረው እየፆሙና እየጸለዩ ይሰነብታሉ።ችግራቸው ገፍቶ በተአምራት ድነው ጤነኛ ሲሆኑ ግን ወዲያውኑ ወደ ኋላ መሸሽ ይጀምራሉ። ባሸበሸቡት እጃቸው ሲደንሱበት፣ በዘመሩበት አንደበት ሲዘፍኑበት ይገኛሉ። ትናንት ያስቀደሱባቸው ፣የተጠመቁባቸውን አድባራትና ገዳማት በዕለት ሳይሆን በወርና በዓመትም መሳለም ያቆማሉ።ዓላማው ጊዜያዊ ሲሆን የሆነና  ችግሬ ይፈታ ብቻ ብሎ የሚቀርብ ወጣት መጨረሻው እንዲህ ይሆናል።ምንም እንኳን ለጊዜው የቀረበበት ምክንያት ችግሩ ቢሆንም  ልቡ ተሰብሮ መንፈሳዊ የሆነና ስለመንግሥተ ሰማያት ማሰብ የጀመረ  ወጣት ግን ጥቂት ገንዘብ የሚያገኝበት ሥራ አይደለም በጣም ብዙ ሀብት በእጁ ቢገባ እንኳን ከእግዚአብሔር ቤት አይርቅም።
የውጭ ፕሮሰስ ጀምረው ቪዛው እጃቸው እስኪገባ ላገኙት ታቦት፣ ለገጠማቸው ቤተክርስቲያን የሚሳሉ ወጣቶች ጥቂቶች አይደሉም።ቪዛው እጃቸው የገባ ዕለት ሻማ አብርተው እልል ይላሉ። ወደ አየር መንገድ እስኪሸኙ ካሰቡበት ሀገር  ገብተው  ቁርጣቸውን እስኪያውቁ ከቦርሳቸው ጸሎት መጽሐፍ አይለይም።ሁሉም አልፎ የባሕር ማዶውን ኑሮ ሲጀምሩ ግን ክርስትናቸው የስንፍና ጥላ ያጠላበታል። ከመንፈሳዊነት ይልቅ የሀገር ቤቶች ዘፋኞች በሚያቀርቧቸው የመዝናኛ ዝግጅት ላይ መታደምን መዝናናትን ይመርጣሉ። ሁሌ ጭፈራ ሁሌ አስረሽ ምችው ይሆናል።
አንተም እንዲህ እንዳትሆን ራስህን ጠይቅ።ተቸግረህ ተጨንቀህ  የነበረህን መንፈሳዊ ጥንካሬ ይዘህ  ለሁል ጊዜውም ቀጥል።ከአበው አንዱ የሆነው አባታችን ያዕቆብ እንዲህ ይላል”አባቶቼ አብርምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር ፣ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፣ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፣እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ያባርክ።”/ዘፍ48-15/ይህ ትናንትን  ካልዘነጋ  መንፈሳዊ ሰው የሚወጣ የእምነት ቃል ነው።አንተም እንደዚሁ ስለትናንተና  ጉዞህ አስብ።የተደረገለህን ፈጽመህ ላለመርሳት ሞክር።የኤርትራ  ባህርን ያሻገረ ፣ከፈራኦን እጅ ያዳነ ፈጣሪ መረሳት የለበትም።ሁል ጊዜም ችግርህን መከራህን በእሳትና በውሃ መካከል ያለፍክበትን ዘመን አትርሳ።ያን ጊዜህ ጉዞህ ዓላማ ያለው መንፈሳው ጉዞ ይሆናል።
እል 
መናፍቃን ተፈታትነውት፣የአንተ ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ መቼ ይሰበክባታል ብለውት ተበሳጭቶ የሚመጣም ወጣትአለ። መናፍቃኑ ማርያም ታማልዳለች ብለህ ታምናለህ እስኪ ካመንህ መልሱን ንገረን የት ላይ ነው የተጻፈው ብለው ሲያዋክቡት ለጊዜው ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ  ያጣል።መልስ በማጣቱ ተቆጥቶ ወደቤተ ክርስቲያን ይመጣል።መናፍቃንንለማንበርከክ አፋቸውን  ለማስያዝ ወደ ቤተክርስቲያን  ይቀርባል።ሰባኪው ወጥቶ ሲሰብክ ስለእመቤታችን አማላጅነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሶ ካስተማረ ጥቅሱን በጥንቃቄ ይይዛል።የሚይዘው ሊማርበት ሳይሆን መናፍቃንን ሊከራከርበት ነው።በዚህ ሁኔታ የተወኑ ጥቅሶች ከሰበሰበ በኋላ በየመንገዱ እየዞረ መናፍቃን አዳኝ ተከራካሪ ይሆናል። እንዲህ ያለ ወጣት ለድኅነት ስለማይማር ወደ ቤተ ክርስትያንም የሚመጣው ለክርክር  ብቻ ስለሆነ መንፈሳዊነት ፆሙ ፣ጸሎቱ፣ ንስሐው፣ቁርባኑ ፈጽሞ ላይታሰበው ይችላል።ለእርሱ ሃይማኖት ማለት ክርክር ማለት ነው።እልኩን እስካልተወጣ እረፍት አይኖረውም።
 መናፍቃንን ለመርታት በእነርሱ ውስጥ ያለውን ክፉ መንፈስ ለማሸነፍ መጀመሪያ በበቂ ሁኔታ መማር ሕይወትን ማስተካከል መንፈሳዊ መሆን ያስፈልጋል።”መጋደላችን  ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም።ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር  ከዚህም ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።ስለዚህም በክፉው ቀን  ለመቃወም ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። ድል እንድትነሱ በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ኤፌ 6-12 ይላል። ክርክሩ ከሰዎች ጋር አይደለምና እነርሱ ጥግ አድርጎ ከሚመጣ ክፉ መንፈስ ጋር ነው።ይህንን ክፉ መንፈስ ድል ለመንሳት ደግሞ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊነት ያስፈልጋል። ሠለስቱ ምእት አርዮስን ለማውገዝ በኒቂያ ሲሰበሰቡ ከሁሉ በፊት ሱባኤ ገብተው ነበር።አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዘግተው መስከረም ሃያ አንድ ቀን ነው ከሱባኤ ወጥተው ድል የነሱት።በመንፈሳዊነ ኃይል ስለቀረቡ አሪዎስ ለጠየቃቸው ጥያቄቆች በቂ መልስ ሰጥተው የቤተክርስቲያኒቱን ክብር አስጠብቀው ጉባኤውን በድል አጣናቀዋል።አንተም በየመንገዱ መናፍቃንን  ከመከራከርህ በፊት ራስህን ቀይር። ዓላማውህ ክርክር ሳይሆን ገነት መንግሥተ ሰማያት ይሁን።ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ።
አንድ ወጣት ትዝ ይለኛል ቤተክርስቲያን ሲመጣ በመናፍቃን ምክንያት ነው።ኋላ ጥቂት ጊዜ ተማረና ክርክር ጀመረ። መናፍቃንን እየተከታተለ መከራከሩን ቀጠለ። አባቶች እንዲተው መከሩት መጀመሪያ ተቀምጠህ ተማር አሉት።አልሰማቸውም በዚህ መልኩ ስድስት ሰባት ወር ያህል ሲከራከር ከቆየ በኋላ ከእነርሱ ተከራክሮ ሲመለስ ተደበላልቆበት የተመረዘ ሀሳብ ይዞ ይመጣ ጀመር።ግማሽ የፕሮቴስታንት፣ግማሽ የኦርቶዶክስ ሃሳብ ይዞ መጓዝ ጀመረ።ጓደኞቹ ሲያነጋግሩት አንዳንድ ጊዜ የሚናገረው ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚጋጭ ስለሆነ መግባባት አቃታቸው።ተው ቢሉትም ክርክር ስለሚወድ ከእነርሱም ጋር መከራከር ጀመረ።ይህ ልጅ እያለ እያለ ተደባልቆበት ጭንቅላቱ እስከመበላሸት ደርሶ ወደ አንድ የጠበል ቦታ ተወሰደ።ሁሉን መደባለቅ ሳይጸኑ ሳይበረቱ ለክርክር መዘጋጀት መጨረሻው አስቸጋሪ ነው።
    መናፍቃንን በማሰብ መጥተህ ከሆነ  ወደፊት የነርሱን ነገር ብቻ በማሰብ ላለመድከም ሞክር።ከሁሉ በፊት ራስህን አድን።የጠራህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው እንዳለ አትርሳ።ሌሎችን ለማዳን መጀመሪያ አንተ ብርቱ ሁን።መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ ለሌሎች መልስ ለማግኘት ሳይሆን ለአንተ ሕይወት የሚጠቅመውን ለመውሰድ ይሁን።የእልኸኝነት ጉዞህን በመንፈሳዊነት ተካው።
         ይቆየን