ዓርብ 8 ኦገስት 2014

ፆመ ፍልሰታ እና በረከቱ በቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው


የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

በገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ቀን ፳፻ ዓ.ም.)፡- በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጠፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡
፩. ንጽሕት ነሽ፤ ብርህት ነሽ፡፡ በአፍአ በውስጥ ንጽሕት ነሽ፡፡ ሊቁ “ዲያተሳሮን” በተባለው የወንጌል ትርጓሜ መጽሐፉ የእመቤታችንን ንጽሕና ሲናገር፡- “የማርያም ሰውነት የምድር ላይ መቅደስ ነው፡፡ በዚሁ መቅደስም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኀጢአት፣ በሞትና በርግማን ፈንታ የበረከትን ዘር ሊዘራ መጣ፡፡ የኤልሳቤጥም ሰላምታ ይህንን አረጋገጠ፡፡… አንተና እናትህ ብቻ በማንኛውም ረገድ ንጹሐን ናችሁ፡፡ ጌታ ሆይ! በአንተ ውስጥ ምንም ነቅዕ የለም፤ በእናትህም ውስጥ ምንም ምልክት የለም” ብሏል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatesaron, pp 91-92/፡፡

 ጌታን በማኽል እጅሽ የያዝሽው ሆይ! ምልዕተ ክብር ሆይ! (ተፈስሒ) ደስ ይበልሽእያሉ ፍጥረት ኹሉ ከአንቺ ጋር ደስ ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ከአንቺ ጋር አንድ ባሕርይ ቢኾን ባለሟልነትን አግኝተሻልና (ተፈስሒ) ደስ ይበልሽ፡፡ ግርምት ድንግል ሆይ! ክብርሽን ገናንነትሽን ዕፁብ ዕፁብ እያልን እናመሰግናለን (እናደንቃለን)፡፡ ከማኅፀንሽ ፍሬ የባሕርያችን ድኅነት ተገኝቷልና ከመልአኩ ጋር እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ የማኅፀንሽ ፍሬ ከአባቱ ጋር አስታርቆናልና እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርብልሻለን፡፡ ሊቁ ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ፡- “… መልአኩ ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፡፡ ወደ እርሷ ገብቶም “እነሆ ድንግልናሽ ሳይነዋወጽ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት/ሉቃ.፩፡፴፩//፡፡ ይኸውም በሥጋ ተገልጦ ሊመጣ ስላለው ስለ አካላዊ ቃል ሲናገር ነው፡፡ ሲነግራት “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት እንጂ “ኢየሱስ የተባለው” እንዳላላት ልብ በሉ፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ወልደ እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ የሚድኑበት ስም መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ማለት በዕብራይስጥ “መድኅን” ማለት ነውና፡፡ መልአኩ “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ሲላት መድኅን ትዪዋለሽ ማለቱ ነው፡፡ ለምን? ሕዝቡን ኹሉ ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና” ብሏል /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ ከአባቱ ጋር ካስታረቀን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፪. አባ ሕርያቆስ፡- “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ኾኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ኹሉ በእውነት ተመለከተ፤ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፡፡ የአንቺን መዓዛ ወደደ፤ የሚወደው ልጁንም ወደ አንቺ ሰደደ” እንዲል /ቅዳ.ማር. ቁ.፳፬/ እንደ ሰርግ ቤት አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻልና፤ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ለብሷልና አንድም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ከልክሎሻልና ኃይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ከልሎሻልና ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን /ሃይ.አበ.፻፲፡፳፱/፡፡ ሰው ኾኖ ከኃጢአት አዳነን /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና ከዳዊት ሥር የተገኘሽ ባሕርይ አንቺ ነሽ /ሉቃ.፩፡፴፪/፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ከአብ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ አካል ዘእም አካል የተወለደ፣ ተቀዳሚ ተከታይ (ታላቅም ታናሽም) የሌለው አካላዊ ቃል ባሕርዩን በሥጋ ሠወረ፡፡ ከአንቺም አርአያ ገብርን ነሣ /ፊል.፪፡፯/፡፡
 ከእናንተ መካከል፡- “አካላዊ ቃል አርአያ ገብርን ነሥቶ (የባሪያን መልክ ይዞ)በሰውም ምሳሌ ኾኖ ራሱን ባዶ አደረገ ሲል ምን ማለት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ራሱን ባዶ አደረገ ሲል የእኛን ባሕርይ ገንዘብ ባደረገ ጊዜ ባሕርየ መለኮቱ ተለውጧል ማለት አይደለም፡፡ ባሕርየ መለኮቱን ትቶ መጣ ማለትም አይደለም፤ በፈቃዱ ደካማ ባሕርያችንን ገንዘብ አደረገ ማለት ነው እንጂ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ራሱን ባዶ ያደረገው በመቅድመ ወንጌል “ከጥንት ዠምሮ በባሕርያችን እስኪሠለጥን ድረስ ሰይጣን በተንኰል በሥጋ ከይሲ እንደተሠወረ፤ እኛም ከፍዳ መዳናችን ቃለ እግዚአብሔር በባሕርያችን በመሠወሩ ኾነ” ተብሎ እንደተጻፈ የእኛን ባዶነት በጸጋው ለመሙላት ነው፡፡ ሰው የኾነው እኛን አማልክት ዘበጸጋ ያደርገን ዘንድ ነው፡፡” የባሪያውንመልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ኾኖ ስለ እኛ ብሎ ራሱን ባዶ ካደረገ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፬. አደፍ ጉድፍ ሳይኖርብሽ አምልክን የወለድሽው እመቤታችን ሆይ! በኃጢአት ብርድ የተያዘውን ዓለም ኃጢአቱን ያርቅለት ዘንድ ፀሐየ ጽድቅ ጌታ ከአንቺ ተወልዷልና፤ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንደተናገሩም ዘር ምክንያት ሳይኾንሽ፣ መለወጥ ሳያገኝሽ ወልደሸዋልና ከምድር በላይ ያለሽ ኹለተኛ ሰማይ አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጲያዊው ቄርሎስም፡- “ኦ ሰማይ ዳግሚት ዘወለደቶ ለፀሐየ ጽድቅ ዘውእቱ ብርሃነ ቅዱሳን ዘሰደዶ ለጽልመት - ጨለማን ያሳደደውን (ያስወገደውን) የቅዱሳን ብርሃን የሚኾን አማናዊ ፀሐይን የወለደች ኹለተኛይቱ ሰማይ ሆይ! …” እያለ ያወድሳታል /አርጋኖን ዘረቡዕ/፡፡ ዘር ምክንያት ሳይኾንሽ ከወለድሽው ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ የተሠወረ መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መተርጕማኑ ይህን የበለጠ ሲያብራሩት፡- “ድንኳኗ የእመቤታችን ምሳሌ፤ ቅድስት የነፍሷ፤ ቅዱሳን የሥጋዋ፤ ታቦቱ የመንፈስ ቅዱስ፤ ጽላት የልቡናዋ፤ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷ፤ ቅድስት የልቡናዋ፤ ታቦት የማኅፀኗ፤ ጽላት የትስብእት፤ ቃሉም የመለኮት ምሳሌ ነው” ይላሉ /ውዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ ፻፸፬/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሐሙስ ላይ፡- “ተፈሥሒ ኦ ደብተራ ብርሃን ማኅደሩ ለዐቢይ ሊቀ ካህናት - የታላቁ ሊቀ ካህናት ማደርያ የብርሃን ድንኳን ሆይ! ደስ ይበልሽ” በማለት የሊቀ ካህናት የባሕርይ አምላክ የክርስቶስ እናት አማናዊት ድንኳን መኾኗን አስተምሯል፡፡  
 አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ አድኖናልና ሰው ኾኖ ያዳነን የነባቢ በግዕ (የሚናገር በግ የክርስቶስ) እናቱ ደስ ይላታል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፮. እርሱን ከወለድሽ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኑረሻልና የክርስቶስ እናቱ ተባልሽ፡፡ ድንቅ በሚያሰኝ ተዋሕዶ አማኑኤልን ወልደሸዋልና ባለመለወጥ አጸናሽ፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለማንም ሴት ያልተሰጠ ለድንግል ማርያም ብቻ የተሰጠ ድንግልና ከእናትነት ጋር አስተባብራ ስለ መገኘቷ ሲገልጥ “ወሰቦሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልና፣ ዘእንበለ ርኩስ ከመ በፀንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ - ከድንግል ተወለደ፤ በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋ ያለመለወጥ አጸና፡፡ ድንቅ የሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ስትወልድው ማኅተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ጌታም ሰው ሲኾን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ እርሷ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል እንደምትኖር አካላዊ ቃል ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ሲባል የሚኖር የመኾኑን የተዋሕዶ ልዩ ምሥጢርን ያወቅንባት የተረዳንባት እርሷ ብቻ መኾኗን አስተምሯል /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፯. ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት፣ በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖት ሎዛ ያያት የወርቅመሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲-፳፪/፡፡ ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን በተፈትሖ በማይታወቅ በማኅፀንሽ ችለሸዋልና እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰዋስው (አማላጅ) ኾንሽን፡፡ እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፰. ጽርሐ ንጽሕት ሆይ! እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ኹሉ በቸርነቱ ብዛት ያድን ዘንድ ከአንቺ ተወለደ፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ነውና በአፍአ በውስጥ እናመስግነው፡፡ቸር ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፱. አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ድንግል ምልዕተ ክብር ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእናትሽ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ጠብቆሻልና የዓለም ኹሉ መክበሪያ ንጽሕት ጽዋዕ ነሽ (ከሥላሴ ለምንጠጣው ክብር ምክንያት አንቺ ነሽ)፡፡
 እንደ ደብተራ ኦሪቷ ማለትም ሙሴና አሮን በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት አብርተው በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት እንደሚያጠፏት ፋና ያይደለሽ የማትጠፊ ፋና ነሽ /ዘጸ.፳፭፡፴፩-፵/፡፡
 እንደ ቀደመችው የኦሪት ቤተ መቅደስ ያይደለሽ የማትፈርሺ መቅደስ ነሽ /፩ኛ ነገ.፯፡፵፰-፶/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “አንቲ ውእቱ መቅደስ ዘሐነጸ ሰሎሞን ወአስቀጸላ በሜላትሮን ወለበጠ ዳቤራ በውሳጥያተ መቅደስ፤ … - ሰሎሞን ያሠራት እንደ ዝናር እንደ ዐምድ ባለ ወርቅ የጠፈሯን ዙርያ ያስጌጣት፤ በመቅደስ ውስጥ ያለቺውን ቅድስተ ቅዱሳንዋን ዐውደ ምሕረቷን ግድግዳዋን በጥሩ ወርቅ ያስጌጣት፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፤ ክንፉ ዐሥራ አምስት ክንድ የሚኾን ኪሩብን በውስጧ ያሣለባት ቤተ መቅደስ አንቺ ነሽ” በማለት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች እመቤታችን ሰሎሞን ባሠራት የወርቅ ቤተ መቅደስ መስሎ ኹለንተናዋ በንጽሕና በቅድስና ያጌጠች የተዋበች መኾኗን አስተምሯል /አርጋኖን ዘዐርብ/፡፡ ዳሩ ግን እመቤታችን በንጽሕናዋ በቅድስናዋ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ብትመሰልም ሊቁ (ኤፍሬም) እንዳለው ክብሯ የላቀ ነው፤ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ናትና የማትፈርስ መቅደስ ናት /መዝ.፹፮፡፩-፭/፡፡
 የማትለወጥ የቅዱሳን ሃይማኖታቸው (ቅዱሳን የሚያምኑበት ክርስቶስን የወለድሽላቸው አንቺ) ነሽ፡፡ ድንግል ሆይ! በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ይቅር ይለን ዘንድ፣ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከልጅሽ ዘንድ አማልጅን፡፡ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!