2014 ጁላይ 14, ሰኞ

ክርስትናና ወጣትነት/ክፍል ሁለት/


   በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን        
 ባለፈዉ ዝግጅት በወጣትነት በቤተ ክርስቲያን ስንኖር ልንይዛቸው የሚገቡ መንፈሳዊ ሀብታት ምን እንደሆኑ በየተራ ለመመልከት ቀጠሮ ይዘን ነበር።ዛሬ የመጀመሪያዉን ክፍል እነሆ።
            1-ዓላማ
        ወደ ሰንበት ት/ቤት ስትመጣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትቀርብ የተለያየ ዓላማ ይዘህ ሊሆን ይችላል።ጽድቅ መንግሥተ ሰማያት የሚለው የክርስትና ጉዞ ፍፃሜ ለጊዜው አይታይህ ይሆናል። እያደር ግን መብሰል  ጉዞህን በዓላማ ማድረግ ይገባሃል።ጥሩ ድራማ ተሰርቶ ለሕዝብ የቀረበ ዕለት፣ በመድረክ ላይ የሚቀርበውን ዝግጅት ለማየት ብቻ ሰ/ት/ቤት ብትገባ።በዚያም ተማርከህ ድራማውን ሲተውኑ እንደነበሩት ወጣቶች ለመሆን የሰንበት ት/ቤት አባል ሆነህ ብትመዘገብ። ለጊዜው አይደንቅም።ምክንያቱም ባየኸው ዝግጅት በመሳብህ ጊዜያዊ  ዓላማህ አባል ሆኖ ሌሎችን ያደነቅህበትን መድረክ አግኝተህ  መደነቅ ሊሆን ይችላልና ነው።ዘማሪው በመድረክ ሲዘምር ሕዝቡም የእርሱን መዝሙር  ተከትሎ ሲያሸበሽብ አይትህም ዘማሪ ለመሆን ወደ ቤተክርስቲያን ልትቀርብ ትችላለህ።በሰባክያን የስብከት መርሐ ግብር የሚሰበሰበው ሕዝብና የሚያደንቃቸውን ምዕመን ተመልክተህም ወጣት ሰባኪ ለመሆን ተመኝተህ ይሆናል።ባህታዊ ስትመለከት ብህትውና፣መነኩሴ ስታይ ምንኩሰና፣ በቄስ መስቀል ስትባረክ ክህነት /ዲቁና ፣ቅስና /፣ታይቶህ ይሆናል።በቤተክርስቲያን አካባቢ  ስላሉ አገልጋዮች ብለህ እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ብቻ መንፈሳዊ ብትሆን ለጊዜው አይደንቅም።ይህ አካሄድ ስህተት ቢሆንም በብዙ የወጣቶች ሕይወት ውስጥ የሚታይ የስሜት ጉዞ ነው።
         የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከተለያየ ግብር ሲጠራቸው እርሱን የተከተሉት ማን እንደሆነ ተረድተው ብቻ አልነበረም ። የያዕቆብና የዩሐንስ እናት “ረሲ ሊተ ይንብሩ እሉ ደቂቅየ ክልኤሆሙ አሐዱ በየማንክ ወአሐዱ በፀጋምከ በመንግስትከ። እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግስትህ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ ያለችውም ለዚህ ነው/ማቴ 20-20/።በኢየሩሳሌም ሲነግስ ልጆቿን ግራዝማች ቀኝ አዝማች እንዲያደርግላት ሽታ ነው። ጌታችን ለዚህ ልመናዋ የመለሰላት መልስ “ኢተእምሩ ዘትስእሉ።የምትለምኑትን አታውቁም።”የሚል ነው። ምክንያቱም የእርሱ መንግሥት በመስቀል ላይ ስለሆነ በግራና በቀኝ ካንተ ጋር ይሁኑ ማለት በግራና በቀኝ በቀራንዮ ይሰቀል ብሎ መጠየቅ ነበርና ነው።
  
                 ያዕቆብን ዮሐንስን በእናታቸው በኩል ላቀረቡት ለዚህ ሥጋዊ ጥያቄ በተለያየ ጊዜ መልስ ተሰጥቷቸዋል።በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጦ፣አሳይቶ ሰማያዊ ንጉስ እንጂ ምድራዊ ንጉስ አለመሆኑን አስረድቷቸዋል/ማቴ 17-1/።በጌቴሴማኒ በምሴተ ሐሙስም ንግስናው በመስቀል ላይ መሆኑን አብረውት ሆነው እንዲረዱ አድርጓቸዋል/ሉቃ 22-39/።ሌሎችም ደቀ መዛሙርቱ ከርደተ መንፈስ ቅዱስ በፊት ከመካከላችን ታላቅ ማነው በሚል እርስ በእርስ ተነጋግረዋል።ድውይ  ፈወስን አጋንንት አወጣን ብለው በመደሰታቸውም ስማችሁ በሰማይ መዝገብ ሰለተጻፈ ደስ ይበላችሁ እንጂ አጋንንትን ስላወጣችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ የተባሉበትም ጊዜም አለ። ለጊዜው የተጠሩበትን እስኪያስተወሉት ያስደስታቸው የነበረው ምድራዊ ክብር ብቻ ነበር።ጌታችንን ተከትለው የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ሲመለከቱ፣በጾምና በጸሎት ጸንተው በፀጋ መንፈስ ሲጎበኙ ግን ይህ ሁሉ ቀርቶላቸዋል። ፍሩሃን የነበሩ ጥቡዐን ሆነዋል።ቀድሞ ያልተገለጠላቸው ምስጢር እያደር ተገልጦላቸዋል።
              መንፈሳዊ ሕይወት እንደዚህ ነው አመጣጣችን ከየትም ይሁን ከየት የመጣንበት ዓላማም የተቃናም ይሁን የተንጋደደ እያደር ግን መብሰል ያስፈልጋል።ትላንት ያስደስተን የነበረው በመድረክ ቆመን መዘመራችን፣መስበካችን፣ድራማ መሥራታችን መንፈሳዊ መባላችን፣ በጎረቤት በቤተሰብ ጾመኛ ናት፣ጸሎተኛ ናት፣የቀራት ገዳም የለም ፣ቆራቢ ነው መባላችን ይሆናል። ዛሬ ግን ሊያስደስተን የሚገባው የክርስትና ጉዞአችን ፍጻሜ የሆነው መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ መጠራታችን በእመቤታችን ምልጃ በቅዱሳን እርዳታ በገነት ለመኖር መጠራታችን ሊሆን ይገባል።
            አንዳንድ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመቀማት የመጡም ተመልሰው መንፈሳዊ ይሆናሉ።ለዘረፋ መጥተው ባህታዊ የሚሆኑ አሉ፡፡አንጣዎስ አሞራዊ የቤተ መቅደስ ገንዘብ ሲቀማ ይኖራል።ከዕለታት አንድ ቀን እንደ ልማዱ እቀማለሁ ብሎ ሲሄድ መላእክት ተገልጠው እሳት አዝንመውበታል። ሐፀ እሳት ኩናተ እሳት እየወረወሩ ወጉትም ይላል። በዚህ ምክንያት ይህ ሰው ከጥፋቱ አምኗል ተጠምቋል።/በሰማእትነትም አርፏል/ማር ይስሐቅ ገጽ 55፣ስንክሳር ነሐሴ 17/።ቅዱስ ጳውሎስ ሳውል ተብሎ ሲጠራ ሳለ ጌታችንን አሰቅሎ ፣ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ አስቀጥቅጦ ይህ አልበቃ ብሎት ሌሎች ደቀመዛሙርትን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ተጓዘ ። ለፈሪሳዊያን ሕግ ቀንቶ በሐዋርያት ላይ ሰይፉን መዘዘ።በዚህ ጊዜ ነው በመንገድ ጌታችን ተገልጦ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ? የመጊያውን ብረት ብትቃወም ባንተ ይብስብሃል ያለው።ይህ  የጌታችን ተግሳፅ አሳዳጅ የነበረውን ተሳዳጅ ፈሪሳዊውን ክርስቲያን አድርጎታል /ሐዋ 9-1/።እነዚህ በርቀት ከክርስትናው ውጭ የነበሩ አበው በእግዚአብሔር ቸርነት እውነታውን ተረድተው ከተመለሱ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለህ አንተማ የመጣህበትን ጊዜያዊ ዓላማ ትተህ ለዘላቂው ዓላማ /ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት/ የማትዘጋጅበት ምክንያት አይኖርም።    
            እንደ ሐዋርያት ለጊዜው ያልተረዳኸው ጉዳይ ቢኖር እንኳ የኋላ ኋላ መንፈሳዊውን ሕይወትን መሻቱ ካለህ መንፈሳዊ መሆንን ገንዘብ ማድረግ አይከብድህም።በመንፈሳዊ ሕይወት እየበሰልክ ጊዜያዊውን ትተህ ዘለዓለማዊውን እያሰብህ ካልሄድህ ግን ክርስትናህ ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል።ሁል ጊዜ ወተት የምትመኝ ጥሬ ወደ መቆርጠሙ የማትደርስ ፣ሁል ጊዜ ለዝናና ለክብር የምትሮጥ፣ ሰማያዊውን ሕይወት የማትናፍቅ ከሆነ ግን ጉዞህ አጠያያቂ መሆኑ የማይቀር ነው። ቅዱስ  ጳውሎስ የገላትያንን ምዕመናን ከዕለት ዕለት አልሻሻል ከትናንት ዛሬ አልቀየር ቢሉት ወቅሶአቸዋል። “ኦ አብዳን ሰብአ ገላትያ መኑ አሕመመክሙ ከመ ኢትእመኑ በጽድቅ ዘያስተርኢ ለዐይን ኢየሱስ ክርስቶስ።እናንተ ዐላዋቆች የገላትያ ሰዎች በምታዩት በአማናዊዉ መሢህ በክርስቶስ እንዳታምኑ ማን ተመቀኛችሁ።ዘአቅደመ ተጽሕፎ በእንቲአሁ።እንዲወለድ አስቀድሞ የተነገረለት።ከመሂ ይሰቀል።እንዲሰቀልም/የተነገረለት/” ብሏቸዋል/ገላ 3-1/።
            ከዚህ አንፃር  በጉዞህ ዓላማ ሊኖርህ ይገባል።የትላንቱን ትተህ ዛሬን በመሻሻል ስለ ክርስትና ጉዞ ፍጻሜ ማሰብ ይኖርብሀል።  አንድ ሰው ዲያቆን ቢሆን ቄስም ቢሆን ዘማሪም ቢሆን ሰባኪም ቢሆን ይህ የክርስትናው ፍጻሜ አይደለም። እነዚህ ሁሉ በክርስትና ጉዞ የሚያገኛቸው ነገሮች ናቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርገውን ጉዞ ለማቅናት የሚያግዙት መንፈሳዊ ሥጦታዎች ናቸው።እነዚህን ይዞ በመንፈሳዊነት ከበረታ ለክብር የበቃል።አስተውል አንተም ሥጦታህን አክብረህ ፀጋህን አውቀህ በአገልግሎት ከበረታህ በመንፈሳዊነት ከፀናህ በመጨረሻ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ክብር ትበቃለህ።አለበለዚያ ግን ፀጋህን ካላወቅህበት የትኛውንም ያህል ብታገለግል ከወቀሳ አትድንም።
            በወንጌል “እግዚኦ እግዚኦ በስምከ ተነበይነ ፣ወበስመ ዚአከ ወአጋንንተ አዉጻእነ ፣ወበስመ ዚአከ ኃይላተ ብዙኀ ገበርነ ይብሉኒ። በይእቲ ጊዜ እብሎሙ ግሙራ ኢየአምረክሙ ረሀቁ እምኔየ  ኩልክሙ እለ ትገብሩ ዐመፃ” “አቤቱ አቤቱ በስምህ ትንቢት ተናግረን፣ በስምህ አጋንንት አውጥተን በስምህ ብዙ ተአምራትን አድርገን አልነበረምን ይሉኛል።ያን ጊዜም ፈጽሞ አላውቃችሁም ዐመፅን የምታደርጉ ሁላችሁ ከእኔ ራቁ እላቸዋለሁ/ማቴ 7-22/ ተብሎ ተጽፏል። ከዚህ ምዕራፍ ለአገልግሎት ተብሎ የሚሰጥ ፀጋ ብቻውን ለመንግሥተ ሰማያት ክብር እንደማያበቃ እንረዳለን።ለመንግሥተ ሰማያት ክብር የምትበቃው ከሁሉ አስቀድመህ ጽድቁን የምትሻ ከሆነ ነው። ሲነጋና ሲመሽ፣ስትተኛና ስትነሳ፣ስትቆርብም ንስሐ ስትገባ፣ስትዘምርም ስትሰብክም ፣ሰንበት ተማሪ ስትሆንም፣ በዓውደ ምሕረት ጉባኤ ስትገኝም በየትኛውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ፍፃሜህን የምታስብ ከሆነ ነው።
                ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ሰማዕታት ከዐው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት።ሰማዕታት ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን አፈሰሱ ሰለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ/ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ/ይላል።የሰማዕታት የተጋድሎ ፍፃሜ፣የባሕታዊያን የብሕትውና ኑሮ ተስፋ፣የሊቃነ ጳጳሳት፣ የመነኮሳት፣የቀሳውስት፣የዲያቆናት፣የምዕመናን ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወት ዳርቻ መንግሥተ ሰማያት ናት።በአንደኛውም በሦስተኛውም በስድስት በዘጠኝ በአስራ አንድ ሰዓት የገባው ሁሉ የሚቀበላት አንድ ቢኖር መንግሥተ ሰማያት ናት።
                                                             ይቆየን