የእጅ መንሻ ሥርዓት
ጌታዬ ሆይ የምግባር ድኸ ነኝና ላንተ የማቀርበው እጃ መንሻ የለኝም ነገር ግን ጻድቃን በሚቆርቡበት ጊዜ የሚያቀርቡልህን ፍቅር ስለኔ ሕይወት
ላባትህ ያቀረብኸውን ፍቅር እንደ እጅ መንሻ አድርጌ አቀርባለሁ ላንተ ሞትና ሕማማት መታሰቢያ እንዲሆን
ለእግዝእትነ ማርያም ለጻድቃን ለወዳጆችህ ሁሉ ለኔም ጻጋ ስለ ሰጠህ ምስጋና አቀርብልኻለሁ፡፡
ከዚህም ሌላ ለኔ የኃጢአት ፍትሐት እንድትሰጠኝ
እለምንኻለሁ፡፡በምሞትበት ጊዜ ጸጋህን እንድትሰጠኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ዘዓርብ
ለእግዝእትነ ማርያም ጸሎት
ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት የኢየሱስ ክርስቶስ እናት
ሆይ ባንቺ የተፀነሰን አምላክ እኔ ዛሬ የምቀበለው ነኝ አንቺ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንድትሆኚ ሌላ ኃጢአት በሰው ሁሉ የደረሰ
የአዳም ኃጢአት ስንኳአልደረሰብሽም፡፡እኔ ግን ኃጢአት የሠራሁ ስሆን ያንቺን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ልቀበል
ወደ ቁርባን እቀርባለሁ፡፡
መሐሪት እናት ሆይ ክፋቴ ብዙ ነውና እርሱን ስቀበል
እንዲምረኝ እያዘንሽ አማልጂኝ የኔ መቀበል ክቡር ልጅሽን ማዋረድ መናቅ እንዳይሆን እርሱን ልጅሽን በምትቀበይበት ጊዜ የተደረገን
ያንቺን መዘጋጀት ያንቺን ትሕትና ያንቺን ንጽሕና ሰለኔ ፈንታ እንድታቀርቢልኝ እለምናለሁ፡፡
ውዳሴ አምላክ
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፈልገህ ከቦታቸው
ልታገባ ልትመልስ የመጣህ አንተ ነህ የጎሰቆልሁ እኔንም ፈልገህ ከሚናጠቁ አንበሶች ወደ ምድንበት ያለ ድንጋፄም በጥላህ ዐርፌ ወደ
ምኖርበት ወደማትፈርስ ቅጽርህ ልታገባኝ ምን ያህል ይገባህ ይሆን አቤቱ በባርያህ በዳዊት ቃል የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ
ክቡር ነው ብለሃልና ጌታዬ ሆይ በኃጢአት ከሚመጣ ሞት አድነኝ ሕይወትና ሥርየትን ስጠኝ በጎ ነገርን ለዘላለም አድርግልኝ አቤቱ
ይድን ዘንድ መመለሱን ነው እንጂ የኃጥኡን ሞት እንዳልወድ መሐላን
ምያለሁ ብለህ በሕዝቅኤል አድረህ ተናግረህ ነበር፡፡
ጌታዬ ሆይ ለሚመለሱት የምትሰጣትን እንዲህ ያለችይቱን
ንስሐ ስጠኝ አቤቱ ንስሐን ከማያሻቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቅን ይልቅ ባንድ ኃጥእ መመለስ በመላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ ይደረጋል
ብለህ አንተ ተናግረሃልና፡፡
ጌታዬ ሆይ በመላእክት ዘንድ እንዲህ ያለ ደስታ
እንዲደረግልኝ ይህቺን የምትመስል ንስሐን ስጠኝ ጌታዬ ሆይ ‹‹ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ወደኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ››ብለህ ተናግረሃል፡፡ አቤቱ ወደ አንተ እንድመጣ
መምጣቱን ስጠኝ ከኃጢአት ሸክም ታድነኝ ዘንድ የዘላለም ዕረፍትን
ትሰጠኝ ዘንድ አሜን ይደረግ፡፡
ጌታዬ ሆይ ኃጥአንን ለንስሐ ልጠራ ነው እንጂ
ጻድቃንን ልጠራ አልመጠሁም ብለህ አንተም ተናግረሃል ጌታዬ ሆይ በደሌንና ኃጢአቴን ይቅር ትለኝ ዘንድ እኔን ኃጥኡን ባጠራርህ ወደ
አንተ እንድመጣ አድርገኝ ጌታዬ ሆይ በነፍስ ከተጎዳ ለሰው ምን ይረባዋል ብለህ ተናግረኻል፡፡ጌታዬ ሆይ ነፍሴን በፊትህ ገንዘብ
እንዳደርጋት አድርግልኝ፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ጎስቋላ ድኻ የምሆን እኔን ይቅር በለኝ እኔ የረከስኩ ያደፍኩ ነኝ እኔ ዘማዊ ነኝ እኔ ክፉ ነኝ
እኔ ጠማማ ነኝ እኔ በኃጢአት የሰጠምኩ ነኝ እኔ መንገድ የጠፋብኝ ነኝ እኔ የተናቅሁ ነኝ እኔ የተዋረድሁ ነኝ እኔ ስለ ክፉ ሥራዬ
ያፈርሁ ነኝ በኔም ያለ ክፉ ሥራዬ ይህ ብቻ አይደለም በደሌ ስለበዛ ዕጥፍ ይሆናል እነጂ፡፡
ክቡር ጌታዬ ሆይ እለምንኻለሁ ለጋስ ሆይ የሠራሁትን ታላቁን ኃጢአቴን ይቅር እንድትለኝ አንተ ታውቃለህና
ከኃጢአት እድፍ ሁሉ አንጻኝ፡፡
ጌታዬ ሆይ እለምንሃለሁ ለኋላ መከራዬ በሠራሁት በጠላትነት ከተነሡብኝ ከጎተቱኝ ልብሴንም ከገፈፉኝ ልብሴንም ከገፈፉኝ ወንበዴዎች ታድነኝ ዘንድ
ከእኔ የወሰዱትን ገንዘብ መልስልኝ በርኅሩኅነትህም ዘይት ቁስሌን አድነኝ አቤቱ ጌታዬ ሆይ በበጎ ይቅርታህና በክቡር መስቀልህ ሰይጣንን
ፈጥነህ ከእግሬ በታች ቀጥቅጠው፡፡አቤቱ በሥልጣንህ ኃይሉን አድክመው ሠራዊቱንም በመላእክት ጉበኞች ከእኔ በትናቸው ከክፉ ሕሊናና
ከመከራም ሁሉ ጠብቀኝ እኔን ባርያህን ከርኩስ ነገር ሁሉ ጠብቀኝ እኔን
ጸጥታንና በቦታ መወሰንንም ስጠኝ የሰይጣንን ፈቃድ እንዳልሠራ በጠላቴ እጅ አትጣለኝ ያ ነገረ ሠሪ እንደወደቀ እንዳልወድቅ
እኔን ባርያህን ተቀበለኝ ወይንህንም ከጠበቅዋት ጋራ ቁጠረኝ የምእመናን ሥራ ሠርቼ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዋጋ ካገኙ ጋራ ዋጋዬን
እንዳገኝ፡፡
አቤቱ በጸራች ንስሐ ዕንባ እንደ አገለገሉህ እንደ
ወንበዴውና እንደ ቀራጩ እንደ ሴሰኛይቱም አድርገኝ አቤቱ የሚያረጋጋ የይቅርታ መልአክን እዘዝልኝ አቤቱ የጠፋች የባርያህን ነፍስ አድነህ ወደማታልፍ መንግሥትህ አግባት የኃጥኡን መመለሱን ነው እንጂ
ሞቱን የማትወድ ሆይ የሚያገለግልህን ልቡና ስጠኝ በአንተ አምኛለሁና ስለ ይቅርታህ ብዛት አንተን ፈለግሁ እንጂ ያለ አንተ ሌላ
የፈለግሁት የለም እኔ ድኻ ችጋረኛ ስለሆንኩ ዘወትር አዝናለሁ፡፡
በሥራዬም ምንም ምን ደስ አላሰኘሁህም፡፡ አቤቱ
ከእንግዲህ ወዲህ የንስሐን መጀመርያ ስጠኝ በረድኤትህም ክበበኝ ድካሜንም በክቡር መስቀልህ አጋዥነት አጽናልኝ ራሴንም ከወደቅሁበት
አንሣው በሠራሁት በኃጢአቴ ብዛት አትቈጣጠረኝ ከኃጢአቴ የሚያነጻ ከአንተ በቀር ሌላ የለምና ጠላት አስቶኝ እኔ በስንፍናዬ ያበላሸኋትን የወይንህን ቦታ አርማት ኮትኩታት፡፡ክብርት ጥምቀትህ ያነጻቻት ምድርህን አትተዋት አሜከላና እሾህ በቅሎባታልና፡፡
ነጋር ግን የዕርቅ መልአክን ላከው ከሰይጣን ሥራና ከርኩስ ሁሉ ዳግመኛ ያነጻት ያጸራት ዘንድ፡፡
እግዚአብሔር ሆይ ጽኑ ኃያል ገናና አንተ ነህና
ላንተ ለዘለዓለሙ ክብር ይገባሃል አሜን በእውነት፡፡
መዝሙረ ዳዊት 69
|
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ