ዓርብ 18 ጁላይ 2014

ክርስትናና ወጣትነት /ክፍል ሦስት/

በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን
ዓላማ
  ካለፈው የቀጠለ 
         አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን በከመ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት ከማሁ ያስተጋብእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት ወበኢየሩሳሌም አግዓዚት እንተ በሰማያት። እናንተ የክርስቲያን ወገኖች ዛሬ በዚህች ዕለት እንደተሰበሰባችሁ እንደዚህ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮንና በሰማይ ባለች  ነጻ በምታወጣ በኢየሩሳሌም ይሰብስባችሁ።”/ቅዳሴ ማርያም ቁ.156/ይላል። በዚህች ዕለት ያለው ቀድሶ ያቆረበበትን ነው ። በዚህች ዕለት በቤተክርስቲያን እንደተሰበሰባችሁ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮን ይሰብስባችሁ ከተፈጥሮተ እደ ሰብእ ነፃ በምትሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊትም ይሰብስባችሁ ሲለን ነው።
            ይህ አባት በመቀጠል ስለመንግሥተ ሰማያት ሲተነትን  “ይህን የእመቤታችንን የምስጋና ቃል እንደሰማችሁ የሕጻናትን ምስጋና ያሰማችሁ።"ይላል። እነዚህ ሕጻናት በዘመነ ሔሮድስ መከራ ተቀብለው ያለፉ ናቸው። እነርሱ ከደረሱበት ማዕረግ ያድርሳችሁ፣ በመከራ ጸንታችሁ እነርሱ ከገቡበት ያግባችሁ ሲል ነው።"ወማሕሌተ ዘመላእክት ዘያጠልል አዕፅምተ እምብዝኃ ጣዕሙ ፈድፋደ።"  የመላእክትነት ምስጋና ያሰማችሁ ከደስታው ብዛት የተነሳ አጥንትን የሚያለመልም በተፈጥሮ ገንዘብ አድርገውት የሚኖሩትን የመላዕክትን  ምስጋና ያሰማችሁ ሲለን ነው። 
           "ያብእክሙ ኀበ ተተክሉ ደባትር ዘነደ እሳት። ሰባት የእሳት መጋረጃ ካለበት።"ነደ እሳት ጌታ የሚያወርሰው ሀብት ካለበት መንግስተ ሰማያት ያግባችሁ።"ኀበ ሀሎ ሊቀ ካህናት።ህየ ሀሎ መልክአ ገጹ ሥዑል፣አክሊል ንጹሕ፣ ወአልባስ ብሩህ ዘኢተኬነዎ እደ እጏለ  እመ ሕያው።አላ ዘእምላዕሉ አንትሙ።የካህናት አለቃ ወዳለበት ያግባችሁ፣የተሳለ የፊቱ መልክ ከዚያ አለ።ንጹሕ አክሊልና ብርህ ልብስ ከዚያ አለ።እርሱም ከላይ የተገኘ ነው የሰው እጅ ያልተጠበበት ነው።"አክሊል ያለው መንግሥተ ሰማያት። አልባስ ያለው እግዚአብሄር  ለወዳጆቹ ለምእመናን የሚያወርሰው ክብር ነው።ለምእመናን የሚያወርሰው ክብር ካለበት  ከመንግሥተ ሰማያት ያግባችሁ።"ያብእክሙ ኀበ ሀለዉ ማኀበረ ነቢያት ቅዱሳን።" ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ ያላቸው የተመረጡ የነቢያት ወገኖች ካሉበት። "ወማኀበረ ሐዋርያት ሰባኪያን "ቃላቸው ወደ ዓለም ሁሉ ወጣ ነገራቸውም እስከ ምድረ ዳርቻ ተሰማ ተብሎ የተነገረላቸው የሐዋርያት ወገን ካሉበት፣ ያግባችሁ። "ወማኀበረ ሰማዕት መዋዕያን።ድል የነሱ የሰማዕታትም ማኅበር ካሉበት ያግባችሁ።ወማኅበረ ጻድቃን ቡሩካን ።ቡሩካን የጻድቃን ወገኖች ካሉበት።ወማኅበረ መላእክት ትጉኃን።ትጉኃን የሚሆኑ የመላእክት አንድነት ካለበት ያግባችሁ።ወማኅበረ ደናግል ወመነኮሳት ፍጹማን ።ፍጹማን የሚሆኑ የመነኮሳት የደናግል ወገኖች ካሉበት ያግባችሁ።ወምስለ ኩሉ ፍጻሜ ማኀበራ ለቅድስት አሐቲ እንተ ላዕለ ኩሉ ቤተክርስቲያን።ከሁሉ በላይ ከሆነች ከአንዲት ቅድስት ቤት ክርስቲያን አንድነትዋ ሁሉ ጋር ያግባችሁ።"ከምእመናነ አሕዝብ በላይ የምትሆን የምእመናን ፍጹም አንድነቷ ካለበት ያግባችሁ። "ወምስሌሆሙ ታቦት ዘዶር እንተ ይእቲ እግዝእትነ ማርያም።ከእነርሱም ጋር ታቦት ዘዶር ወዳለችበት ይህችውም እመቤታችን ናት።"ይላል።የእመቤታችን ምሳሌ የምትሆን ታቦት ዘዶር ካለችበት ከመንግሥተ ሰማያት ያግባችሁ። አንድም የጌታ ማደሪያ የምትሆን የብርሃን ታቦት እመቤታችን ካለችበት ያግባችሁ ሲለን ነው።አባ ሕርያቆስ በሥርዓተ ቅዳሴ ለመሳተፍ የተሰበሰቡ ካህናትንና ምዕምናንን ባንድነት ከላይ ባየነው መልኩ  ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃን ያብቃችሁ ይላል። ምክንያቱም የማስቀደሱም የመቀደሱም፣የመማሩም የማስተማሩም፣ የመዘመር የማዘመሩም፣ የሁሉም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ዓላማ ለመንግሥተ ሰማያት መብቃት ስለሆነ ያንን ሲያዝገነዝበን ነው።
 "
           ቅዱስ አትናቴዎሰም በቅዳሴ ድርሰቱ" ገደል ጉጻጉጽ ቀና ያይደለ ጠማማ የሆነ አገር ከዚህ ያለን አይደለም ነቢያትና ሐዋርያት አስቀድመው የደረሱበት በልዕልና ያለ ነው እንጂ። ለእኛ ከዚሕ በአሸዋ  የተሠራ ነፋሳት የሚነፍሱበት ፈሳሾች የሚገፉት ቤት ያለን አይደለም።በላይ ያለች ነጻ የምታወጣ ኢየሩሳሌም ናት እንጂ። አስቀድመው የጳጳሳት አለቆች፣ ጳጳሳት ፣ኤጴስ ቆጶሳት፣ቀሳውስትና ዲያቆናትም የገቡባት ናት እንጂ። እኚህ እንደኛ ሥጋን የለበሱ ሲሆኑ ባነዋወራቸው መላእክትን መሰሉ።ሰውነታቸውን አነጹ ልብሳቸውንም ነጭ  አደረጉ። የሥጋቸውንም አዳራሽነት አላሳደፉም ስማቸው በበጉ ደም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጻፈ "/ቅዳሴ አትናቴዎስ ቁ.49/ይለናል።በምድራዊ ኑሮ ላይ ብቻ ተደግፎ ሕሊናችን ከመንግሥተ ሰማያት እንዳይርቅ መኖሪያችን ይህ አይደለም ሀገራችን በሰማይ ነው እያለ ይመክረናል።
        ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ነገር ሲጽፍ “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት።ከዚያም ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እሱን  እንጠብቃለን ።”/ ፊሊጲ 3-20 /ብሏል።ሀገራችን በሰማይ መሆኑን ተረድተን በሩቅ የምናያት መንግሥት ሰማያትን ተስፋ እያደረግን  ብንጓዝ በምድር ላይ ያለ ክብር፣ ዝና ፣ሀብት፣ብልጽግና ፣ሁሉም ከጀመርነው ጉዞ አያስቀሩንም።
         ቅዱስ ጳውሎስ መኑ የኀድገነ ፍቁሮ ለክርስቶስ።ከክርስቶሰ ፍቅር  የሚለየን ማነው? የክርስቶስን ፍቅር ማን ያስተወናል? ሕማም ነውን? መከራ ነውን? ስደት ነውን ?ረኃብ ነውን ?መራቆት ነውን ?ሾተል ነውን? ጭንቅ ነውን?ይለናልሮሜ 8-35/። መንፈሳዊ ሰው መከራ ቢፈራረቅበት ችግር እንደ ዶፍ ዝናብ ቢወርድበት ከክርስቶስ ፍቅር አይለየውም በመከራ ውስጥ ሁል  ጊዜ ክርስቶስ በፍርድ ቀን የሚያወርሰውን መንግሥተ ሰማያት ያስባል። በዚህም ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ሲጠራው ለአምላኩ ይታመናል።ሐዋርያው "የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል?እንዴትስ ደጅ ይጠናል? የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን ትዕግሥታችን ይታወቃል። እሱን ተስፋ  አድርገን በእርሱ እንደጸናን መጠን ይለናል/ ሮሜ 8-25/። ክርስቲያን የማይታየውን ዓይን ያላያት ጆሮ ያልሰማት እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ ያዘጋጃትን  መንግሥተ ሰማያትን ተስፋ ማድረጉ ብፁዕ ያሰኘዋል። የማይታየውን ተስፋ አድርጎ በሚታየው ዓለም ላይ የሥጋ ምቾት የዓይን አምሮት መናቁ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ አለማለቱ ብፁዕ ያሰኘዋል።
             አንጢላሪዮስ የተባለ ሰው ባለፀጋ ነበር ነዳይ መጥቶ ከደጁ ይቆማል። ይህን ደሃ ለማባረር አስቦ ድንጋይ ቢያጣ ዳቦ ወርውሮ መታው።ደሃው ርቦት ስለነበር በደሙ የተለወሰውን የተፈነከተበትን ዳቦ አንስቶ ይዞ ይሄዳል።አንጢላሪዮስ በዚያን ሌሊት ራዕይ ተመለከተ። መላእክተ ጽልመት /የጨለማ መላእክት/ ነፍሱን ከሥጋው ለይተው ይዘውት ሲሄዱ ቅዱሳን መላእክት እያዘኑ ተከተሏቸው።የጨለማ መላእክትም ከዚህ ምን  አላችሁ ቢሏቸው ትላንትና የመጸወተውስ ብለው ቅዱሳን መላእክት መለሱ።በዳቦው መታው እንጂ መቼ መጸወተ ተብሎ ደሃው እንዲመሰክር ተጠራ። ያ ነዳይም ትላንትና ያጠገበኝ ይህ ባለ ጸጋ ነው ከረሃቡ ጽናት የተነሳ የፈሰሰኝ ደም አልታወቀኝም ብሎ መስክሮለታል። አንጢላሪዮስ ይህን ራዕይ አይቶ ሲነቃ ምጽዋት ለካ እንዲህ ያጸድቃል ብሎ ያለውን ሁሉ መመፅወት ጀመረ።ራቱን ሳያስቀር መጸወተ።ከዚህ በኋላ ነዳያን ምጽዋት እያሉ ሲያስጀግሩት ጎበዝ ባሪያ አለ ብላችሁ ሽጡኝና ተካፈሉኝ አላቸው።ለሠላሳ ብር ሸጠውት ተካፍለዋል። የመንግስተ ሰማያት ነገር ሲገባው የሰው ልጅ እንዲህ ይሆናል።ሁሉን  ይተዋል ይህን ዓለም እንደ ጉድፍ ይቆጥረዋል።
            የወጣትነታችን  ሕይወት የተባረከ አገልግሎታችንም የሰመረ እንዲሆን  ልንጓዝበት የሚገባን መንገድ ይህ ነው። ልባችንን በመንገዳችን አድርገን ስለመንግሥተ ሰማያት ማሰብ ይገባናል።ልጅ ሳለን እንደ ልጅ አስበን ይሆናል። ዛሬ ግን በማስተዋል መጓዝ ይጠበቅብናል።እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅድስት አርሴማ ፣በወጣትነት እድሜ ሰማያዊውን ክብር ከማሰብ ጋር የክርስትናኝ ሕይወትን መኖር ይኖርብናል።ይህን ሁሉ የሚያደርገው በውስጣችን ያለ ዓላማ ስለሆነ ጉዞአችን በዓላማ ይሁን።
            አንድ የማውቀው ወጣት ትዝ ይለኛል።ቤተ ክርስቲያን በመጣበት ዓመት ስድስት ወር ሳይሆነው ሁሉንም መሆን ተመኘ ሰባኪ ሲመለከት ሰባኪ፣ ዘማሪ ሲያይ ዘማሪ፣ዲያቆን ሲያይ ዲያቆን፣ባህታዊያን ሲያይ ባህታዊ፣ ለመሆን ያልሞከረው የለም በየዕለቱ በየሳምንቱ ሃሳቡን ይቀያይራል።ካሴት ላወጣ ነው፣ ካህናት ማሰልጠኛ ገብቼ ኮርስ ወስጄ ጎበዝ ሰባኪ ልሆን ነው፣ ገዳም መግባት አስቤያለሁ፣ ይላል።እንዲህ ሁሉንም እየተመኘ ለአንድ ዓመት ቆየ።ከዚያ ሁሉም ስላልሆነለት ተበሳጭቶ ከቤተክርስቲያን ተለየ፡ ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከተለየም በኋላ ነጋዴ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ሯጭ የመሆን ሙከራ ያደርግ ስለነበር የሰፈር ጓደኞቹ መቀለጃ ሆነ።  ' ይህ ወጣት መጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ለክብር ለዝና ታዋቂ ለመሆን ቢሆንም ጥቂት አየቆየ ሲሄድ ቢበስል መልካም ነበር። ነገር ግን ነገሮችን ሳያገናዝብ በዚያው በመጣበት ሐሳብ እንደጸና ለዝናና ለክብር ብቻ እንደሮጠ ከቤተክርስቲያን ተለየ።
                        ትክክለኛ ዓላማ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ከተረዳን። በክርስትና ጉዞ ወጣቱ ከመስመር የሚወጣባቸውን የስህተት ዓላማዎች ጊዜያዊ የስሜት ጉዞዎች የትኞቹ እንደሆኑ ቀጥለን እንመለከታለን።
    ዝና
         ይህ ብዙ ጊዜ የወጣትነት ሕይወት ከትክክለኛው ዓላማ ውጭ እንዲሆን የሚደረግ ነው።መታወቅ መደነቅ አንቱ መባል በመፈለግ  በዕንባ የጀመሩትን መንፈሳዊ ጉዞ ለዝና በመሮጥ ብቻ የሚፈጽሙ ጥቂቶች አይደሉም።ዝነኝነትን ጊዜያዊ ዓላማው ያደረገ ሰው በቤተክርስቲያን ሌትና ቀን ሲወጣና ሲወርድ ሲለፋ ሊታይ ይችላል። ድካሙ ግን ከእግዚአብሔር ሰማያዊ ወጋን ለመቀበል ሳይሆን በምድር ላይ አንቱ ለመባል ነው። ፈሪሳዊያን ይህ አይነቱ ችግር ነበረባቸው።በየማዕዘኑ በመጸለይ፣ ሰውነታቸውን በጨው ታጥበው በመውጣት ጾመኛ በመምሰል፣ በልብሳቸው ቃለ እግዚአብሔርን ጽፈው በመዞር፣ ከእነርሱ በላይ መንፈሳዊ እንደሌለ ከእነርሱ በላይ ቀናኢ እንደሌለ ያስቡ ነበር። ጌታችን ማስተማር ሲጀምር ይህንን ለሰው ታይታ የሚደረግ የፈሪሳዊያንን ጉዞ ነቅፎታል።በምትጸልዩበትም ጊዜ እንደግብዞች አትሁኑ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በየሙክራቡና በየአደባባዩ መዓዘን መቆምንና መጸለይን ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን አጡ።/ ማቴ 6-5 /ብሏቸዋል።ዋጋቸውን አጡ የሚለን በምድር ላይ አቦ አቦ መባልን ስለፈለጉ ሰማያዊ ዋጋን አጡ ሲለን ነው።በሌላ በኩል በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ እነርሱ እንደ ጾሙ ሰው ያውቅላቸው ዘንድ ይጠወልጋሉና። ግንባራቸውንም ይቋጥራሉና። መልካቸውንም ይለውጣሉና። እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀበሉ ይለናል። እዚህ ላይ ደግሞ ዋጋቸውን ተቀበሉ የሚለው በምድር በሰው ልጆች ከንፈር ተመጦላቸው ምስጋና ቀርቦላቸው ዋጋቸውን እዚህ ተቀበሉ በሰማይ የሚጠብቃችው ዋጋ የለም ሲለን ነው።
        ዝና ሳንፈልገው ሊመጣ ይችላል። የጌታችን ደቀ መዛሙርት “ነገራቸው ወደ ዓለም ሁሉ ወጣ እስከ ምድርም ዳርቻ ደረሰ “ተብሎ እንደተነገረ መልካም ሥራው በጎረቤት በጓደኞቹ ሊታወቅ ይችላል ይህ በራሱ ስሕተት ሐጢያት ሊሆን አይችልም። ባለቤቱ በልቡ ካልተቀበለው ዝነኛ መሆን ሽቶ የማይሯሯጥ ለሰው ታይታ ብሎ የማይደክም ከሆነ ስህተት አይሆንበትም። ስህተቱ የእግዚአብሔርን መንግስት ረስቶ ለዝና ብቻ ከደከመና ከሮጠ ነው። ሰለዝና ብቻ መጨነቅ የክርስትና ጉዞ ዳርቻ እስከየት ድረስ እንደሆነ እንዳይረዳ ያደርገዋል። ዝነኛ መሆን የሚፈልግ ወጣት ዝነኛ መሆን ካልቻለ የሩጫው ፍጻሜ ይሆንና ሰዎቸ እንዳላወቁት በማሰብ ብቻ ሩጫዬን ጨርኛለሁ ይላል። ምናልባትም የጠበቀውን ዝና ካላገኘ ደግሞ ስለመንግሥተ ሰማያት ስለማያስብ ዝነኛ ካልሆንኩ ምንእሰራለሁ በሚል ቤተክርስቲያንን ጥሎ ይኮበልላል።
          አንድ የማውቀው ወጣት ትዝ ይለኛል።ቤተ ክርስቲያን በመጣበት ዓመት ስድስት ወር ሳይሆነው ሁሉንም መሆን ተመኘ ሰባኪ ሲመለከት ሰባኪ፣ ዘማሪ ሲያይ ዘማሪ፣ዲያቆን ሲያይ ዲያቆን፣ባህታዊያን ሲያይ ባህታዊ፣ ለመሆን ያልሞከረው የለም በየዕለቱ በየሳምንቱ ሃሳቡን ይቀያይራል።ካሴት ላወጣ ነው፣ ካህናት ማሰልጠኛ ገብቼ ኮርስ ወስጄ ጎበዝ ሰባኪ ልሆን ነው፣ ገዳም መግባት አስቤያለሁ፣ ይላል።እንዲህ ሁሉንም እየተመኘ ለአንድ ዓመት ቆየ።ከዚያ ሁሉም ስላልሆነለት ተበሳጭቶ ከቤተክርስቲያን ተለየ፡ ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከተለየም በኋላ ነጋዴ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ሯጭ የመሆን ሙከራ ያደርግ ስለነበር የሰፈር ጓደኞቹ መቀለጃ ሆነ።  ' ይህ ወጣት መጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ለክብር ለዝና ታዋቂ ለመሆን ቢሆንም ጥቂት አየቆየ ሲሄድ ቢበስል መልካም ነበር። ነገር ግን ነገሮችን ሳያገናዝብ በዚያው በመጣበት ሐሳብ እንደጸና ለዝናና ለክብር ብቻ እንደሮጠ ከቤተክርስቲያን ተለየ።
           ሌላ ወጣት ደግሞ አስታውሳለሁ። ወደ ቤተክርስቲያን የመጣው የአንድ ሰባኪ ስብከት ሰምቶ እንደ እርሱ ለመሆን ነው። እንደገባ አካባቢ በየጽዋ ማሕበሩ ካልሰበኩ ለማለት ሞከረ።የሚያውቀውንም የማያውቀውንም እየተናገረ ባልበሰለ ሕሊናው ለመስበክ ሞከረ። የኋላኋላ ግን ወደ ውስጥ እየዘለቀ ሲገባ በገዳማት ያሉ አባቶችን ሊቃውንትን መምህራንን ሲመለከት በራሱ አፈረ። ከዚህ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት በሚገባ ሳላጠና ሕይወቴ ሳይለወጥ አልሰብክም ብሎ መንፈሳዊ ሕይወቱን ብቻ ማስተካከል ቀጠለ፡፤ ለብዙ ዓመታት በንስሃ በፆም በጸሎት ሕይወቱን ፈተሸ። ለመንግሥተ ሰማያት የሚያስፈልገውም መንፈሳዊ ሆኖ መገኘት እንደሆነ ሰለተረዳ እጅግ መንፈሳዊ ሆነ። ኋላ ላይ የስብከት አገልግሎት ፀጋዬ አይደለም እኔ እግዚአብሔርን የማገለግለው አባቶችን በመርዳት ነው በሚል ከደሞዙ አስራት በማውጣት ጓደኞቹን በማስተባበር ሰዎች ሳያውቁበት በየገዳማቱ ያሉ አባቶችን መርዳት ቀጠለ። ይህ ወጣት የመንፈሳዊ ሕይወት ምንነትን ባይረዳ ኖሮ ስብከቱ አልሆን ሲለው ከክርስትናው ይለይ ነበር። መንፈሳዊነት ምን እንደሆነ ስላወቀ በሃይማኖት በምግባር ጸና።የጉዞው ፈጻሜ ለአገልግሎት መድረክ ላይ መውጣት ሳይሆን መንግስተ ሰማያት ለመግባት እስከ ሕይወት ፍጻሜ መጽናት መሆኑን አወቀ።
    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል"የእግዚአብሔር ስም በአንተ እንዳይነቅፍ ከፈለግህ ስለ ዝና አትጨነቅ ። በሌላ በኩል ሌሎች ስላንተ ክፉ እንዲያወሩም መንገድ አትስጣቸው በእነዚህ በሁለት ጉዳዮች ጠቢብ ሁን ።”ስለ ዝናው የሚጨነቅ ሕይወቱ በሁከት የተሞላ ይሆናል። ጸጥታ የልብ መረጋጋት ሰላም አይኖረውም። የገበያ ውጣ ውረድ እንደሚያስጨንቀው ነጋዴ በመታወቅና ባለመታወቅ መካከል ሆኖ ሲጨነቅ ሲጠበብ ይኖራል። ምን ያህል ሕዝብ አወቀኝ? ሰዎች ስለኔ ምን ይላሉ? በሚል ብቻ ሌትና ቀን እንቅልፍ ያጣል።ይህ ደግሞ ረጅሙን ጉዞውን ያስረሳዋል። ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይነጋገር ያደርገዋል።
                                                                     ይቆየን


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ