ዓርብ 8 ኦገስት 2014

የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

በገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጠፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡
፩. ንጽሕት ነሽ፤ ብርህት ነሽ፡፡ በአፍአ በውስጥ ንጽሕት ነሽ፡፡ ሊቁ “ዲያተሳሮን” በተባለው የወንጌል ትርጓሜ መጽሐፉ የእመቤታችንን ንጽሕና ሲናገር፡- “የማርያም ሰውነት የምድር ላይ መቅደስ ነው፡፡ በዚሁ መቅደስም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኀጢአት፣ በሞትና በርግማን ፈንታ የበረከትን ዘር ሊዘራ መጣ፡፡ የኤልሳቤጥም ሰላምታ ይህንን አረጋገጠ፡፡… አንተና እናትህ ብቻ በማንኛውም ረገድ ንጹሐን ናችሁ፡፡ ጌታ ሆይ! በአንተ ውስጥ ምንም ነቅዕ የለም፤ በእናትህም ውስጥ ምንም ምልክት የለም” ብሏል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatesaron, pp 91-92/፡፡

 ጌታን በማኽል እጅሽ የያዝሽው ሆይ! ምልዕተ ክብር ሆይ! (ተፈስሒ) ደስ ይበልሽእያሉ ፍጥረት ኹሉ ከአንቺ ጋር ደስ ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ከአንቺ ጋር አንድ ባሕርይ ቢኾን ባለሟልነትን አግኝተሻልና (ተፈስሒ) ደስ ይበልሽ፡፡ ግርምት ድንግል ሆይ! ክብርሽን ገናንነትሽን ዕፁብ ዕፁብ እያልን እናመሰግናለን (እናደንቃለን)፡፡ ከማኅፀንሽ ፍሬ የባሕርያችን ድኅነት ተገኝቷልና ከመልአኩ ጋር እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ የማኅፀንሽ ፍሬ ከአባቱ ጋር አስታርቆናልና እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርብልሻለን፡፡ ሊቁ ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ፡- “… መልአኩ ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፡፡ ወደ እርሷ ገብቶም “እነሆ ድንግልናሽ ሳይነዋወጽ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት/ሉቃ.፩፡፴፩//፡፡ ይኸውም በሥጋ ተገልጦ ሊመጣ ስላለው ስለ አካላዊ ቃል ሲናገር ነው፡፡ ሲነግራት “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት እንጂ “ኢየሱስ የተባለው” እንዳላላት ልብ በሉ፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ወልደ እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ የሚድኑበት ስም መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ማለት በዕብራይስጥ “መድኅን” ማለት ነውና፡፡ መልአኩ “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ሲላት መድኅን ትዪዋለሽ ማለቱ ነው፡፡ ለምን? ሕዝቡን ኹሉ ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና” ብሏል /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ ከአባቱ ጋር ካስታረቀን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፪. አባ ሕርያቆስ፡- “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ኾኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ኹሉ በእውነት ተመለከተ፤ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፡፡ የአንቺን መዓዛ ወደደ፤ የሚወደው ልጁንም ወደ አንቺ ሰደደ” እንዲል /ቅዳ.ማር. ቁ.፳፬/ እንደ ሰርግ ቤት አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻልና፤ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ለብሷልና አንድም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ከልክሎሻልና ኃይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ከልሎሻልና ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን /ሃይ.አበ.፻፲፡፳፱/፡፡ ሰው ኾኖ ከኃጢአት አዳነን /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና ከዳዊት ሥር የተገኘሽ ባሕርይ አንቺ ነሽ /ሉቃ.፩፡፴፪/፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ከአብ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ አካል ዘእም አካል የተወለደ፣ ተቀዳሚ ተከታይ (ታላቅም ታናሽም) የሌለው አካላዊ ቃል ባሕርዩን በሥጋ ሠወረ፡፡ ከአንቺም አርአያ ገብርን ነሣ /ፊል.፪፡፯/፡፡
 ከእናንተ መካከል፡- “አካላዊ ቃል አርአያ ገብርን ነሥቶ (የባሪያን መልክ ይዞ)በሰውም ምሳሌ ኾኖ ራሱን ባዶ አደረገ ሲል ምን ማለት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ራሱን ባዶ አደረገ ሲል የእኛን ባሕርይ ገንዘብ ባደረገ ጊዜ ባሕርየ መለኮቱ ተለውጧል ማለት አይደለም፡፡ ባሕርየ መለኮቱን ትቶ መጣ ማለትም አይደለም፤ በፈቃዱ ደካማ ባሕርያችንን ገንዘብ አደረገ ማለት ነው እንጂ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ራሱን ባዶ ያደረገው በመቅድመ ወንጌል “ከጥንት ዠምሮ በባሕርያችን እስኪሠለጥን ድረስ ሰይጣን በተንኰል በሥጋ ከይሲ እንደተሠወረ፤ እኛም ከፍዳ መዳናችን ቃለ እግዚአብሔር በባሕርያችን በመሠወሩ ኾነ” ተብሎ እንደተጻፈ የእኛን ባዶነት በጸጋው ለመሙላት ነው፡፡ ሰው የኾነው እኛን አማልክት ዘበጸጋ ያደርገን ዘንድ ነው፡፡” የባሪያውንመልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ኾኖ ስለ እኛ ብሎ ራሱን ባዶ ካደረገ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፬. አደፍ ጉድፍ ሳይኖርብሽ አምልክን የወለድሽው እመቤታችን ሆይ! በኃጢአት ብርድ የተያዘውን ዓለም ኃጢአቱን ያርቅለት ዘንድ ፀሐየ ጽድቅ ጌታ ከአንቺ ተወልዷልና፤ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንደተናገሩም ዘር ምክንያት ሳይኾንሽ፣ መለወጥ ሳያገኝሽ ወልደሸዋልና ከምድር በላይ ያለሽ ኹለተኛ ሰማይ አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጲያዊው ቄርሎስም፡- “ኦ ሰማይ ዳግሚት ዘወለደቶ ለፀሐየ ጽድቅ ዘውእቱ ብርሃነ ቅዱሳን ዘሰደዶ ለጽልመት - ጨለማን ያሳደደውን (ያስወገደውን) የቅዱሳን ብርሃን የሚኾን አማናዊ ፀሐይን የወለደች ኹለተኛይቱ ሰማይ ሆይ! …” እያለ ያወድሳታል /አርጋኖን ዘረቡዕ/፡፡ ዘር ምክንያት ሳይኾንሽ ከወለድሽው ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ የተሠወረ መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መተርጕማኑ ይህን የበለጠ ሲያብራሩት፡- “ድንኳኗ የእመቤታችን ምሳሌ፤ ቅድስት የነፍሷ፤ ቅዱሳን የሥጋዋ፤ ታቦቱ የመንፈስ ቅዱስ፤ ጽላት የልቡናዋ፤ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷ፤ ቅድስት የልቡናዋ፤ ታቦት የማኅፀኗ፤ ጽላት የትስብእት፤ ቃሉም የመለኮት ምሳሌ ነው” ይላሉ /ውዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ ፻፸፬/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሐሙስ ላይ፡- “ተፈሥሒ ኦ ደብተራ ብርሃን ማኅደሩ ለዐቢይ ሊቀ ካህናት - የታላቁ ሊቀ ካህናት ማደርያ የብርሃን ድንኳን ሆይ! ደስ ይበልሽ” በማለት የሊቀ ካህናት የባሕርይ አምላክ የክርስቶስ እናት አማናዊት ድንኳን መኾኗን አስተምሯል፡፡  
 አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ አድኖናልና ሰው ኾኖ ያዳነን የነባቢ በግዕ (የሚናገር በግ የክርስቶስ) እናቱ ደስ ይላታል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፮. እርሱን ከወለድሽ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኑረሻልና የክርስቶስ እናቱ ተባልሽ፡፡ ድንቅ በሚያሰኝ ተዋሕዶ አማኑኤልን ወልደሸዋልና ባለመለወጥ አጸናሽ፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለማንም ሴት ያልተሰጠ ለድንግል ማርያም ብቻ የተሰጠ ድንግልና ከእናትነት ጋር አስተባብራ ስለ መገኘቷ ሲገልጥ “ወሰቦሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልና፣ ዘእንበለ ርኩስ ከመ በፀንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ - ከድንግል ተወለደ፤ በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋ ያለመለወጥ አጸና፡፡ ድንቅ የሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ስትወልድው ማኅተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ጌታም ሰው ሲኾን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ እርሷ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል እንደምትኖር አካላዊ ቃል ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ሲባል የሚኖር የመኾኑን የተዋሕዶ ልዩ ምሥጢርን ያወቅንባት የተረዳንባት እርሷ ብቻ መኾኗን አስተምሯል /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፯. ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት፣ በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖት ሎዛ ያያት የወርቅመሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲-፳፪/፡፡ ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን በተፈትሖ በማይታወቅ በማኅፀንሽ ችለሸዋልና እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰዋስው (አማላጅ) ኾንሽን፡፡ እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፰. ጽርሐ ንጽሕት ሆይ! እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ኹሉ በቸርነቱ ብዛት ያድን ዘንድ ከአንቺ ተወለደ፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ነውና በአፍአ በውስጥ እናመስግነው፡፡ቸር ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፱. አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ድንግል ምልዕተ ክብር ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእናትሽ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ጠብቆሻልና የዓለም ኹሉ መክበሪያ ንጽሕት ጽዋዕ ነሽ (ከሥላሴ ለምንጠጣው ክብር ምክንያት አንቺ ነሽ)፡፡
 እንደ ደብተራ ኦሪቷ ማለትም ሙሴና አሮን በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት አብርተው በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት እንደሚያጠፏት ፋና ያይደለሽ የማትጠፊ ፋና ነሽ /ዘጸ.፳፭፡፴፩-፵/፡፡
 እንደ ቀደመችው የኦሪት ቤተ መቅደስ ያይደለሽ የማትፈርሺ መቅደስ ነሽ /፩ኛ ነገ.፯፡፵፰-፶/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “አንቲ ውእቱ መቅደስ ዘሐነጸ ሰሎሞን ወአስቀጸላ በሜላትሮን ወለበጠ ዳቤራ በውሳጥያተ መቅደስ፤ … - ሰሎሞን ያሠራት እንደ ዝናር እንደ ዐምድ ባለ ወርቅ የጠፈሯን ዙርያ ያስጌጣት፤ በመቅደስ ውስጥ ያለቺውን ቅድስተ ቅዱሳንዋን ዐውደ ምሕረቷን ግድግዳዋን በጥሩ ወርቅ ያስጌጣት፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፤ ክንፉ ዐሥራ አምስት ክንድ የሚኾን ኪሩብን በውስጧ ያሣለባት ቤተ መቅደስ አንቺ ነሽ” በማለት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች እመቤታችን ሰሎሞን ባሠራት የወርቅ ቤተ መቅደስ መስሎ ኹለንተናዋ በንጽሕና በቅድስና ያጌጠች የተዋበች መኾኗን አስተምሯል /አርጋኖን ዘዐርብ/፡፡ ዳሩ ግን እመቤታችን በንጽሕናዋ በቅድስናዋ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ብትመሰልም ሊቁ (ኤፍሬም) እንዳለው ክብሯ የላቀ ነው፤ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ናትና የማትፈርስ መቅደስ ናት /መዝ.፹፮፡፩-፭/፡፡
 የማትለወጥ የቅዱሳን ሃይማኖታቸው (ቅዱሳን የሚያምኑበት ክርስቶስን የወለድሽላቸው አንቺ) ነሽ፡፡ ድንግል ሆይ! በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ይቅር ይለን ዘንድ፣ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከልጅሽ ዘንድ አማልጅን፡፡ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!


ቅዳሜ 2 ኦገስት 2014

ዮሴፍ ፃድቅ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ


አምላክ አሜን!





እንኳን ለቅዱስ ዮሴፍ በዓለ እረፍት በሠላም አደረስዎት!

   
      አባቱ ያዕቆብ እናቱ ደግሞ ዮሐዳ ትባላለች፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ   የእንጨት   ስራ   ባለሞያ  ስለነበር  ቤተሰቡን ያስተዳደር የነበረው በዚህ ስራው ነው ፡፡ በዚህም  የተነሳ ጠራቢው ዮሴፍ  በማለት  አይሁድ  ብዙ  ጊዜ  ስሙት ይጠሩት እንደነበር መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡
     የአራት  ወንዶችና  የሦስት  ሴቶች  ልጆች  አባት ነው፡፡ ማቴ.13፡55 አረጋዊው  ከእመቤታችን  ከቅድስት ድንግል  ማርያም   ጋር   ያለውን   የሥጋ   ዝምድና ስንመለከት፡፡       
 አልዓዛር ማታንነናቅስራነን ወለደ ማታን ያዕቆብን ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ ቅስራ ደግሞ  እያቄምን እያቄም ማርያምን ወለደ፡፡
                                    
     አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ከ1985 አረጋዊያን  መካከል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማገልገል በ84 ዓመቱ ተመረጠ፡፡
የተመረጠውም በሦስት ምስክርነት ነው፡-
1.  በትሩ አብባና  አፍርታ  የእመቤታችን  ጠባቂ  እሱ እንደሆነ ተፅፎባት በመገኘቱ፡፡
2. ርግብ በተለየ ሆኔታ በአረጋዊው በቅዱስ ዮሴፍ  ላይ በማረፏ
3. ዕጣ  ቢያወጡ  ለአረጋዊው  በመውጣቱ  ምክንያት ነው፡፡
    የአምላክን    እናት    ለማገልገልና      በድንጋይ ከመወገር   እንዲጠብቃት    የተመረጠው    አባታችን ቅዱስ ዮሴፍ   በእርጅናው  ወራት   ደከመኝ   ሰለቸኝ ሳይል  አገልግሏል፣  በስደት  ጊዜ  በበርሃ  ተንከራቷል፣ አምላኩን   እንደ   አባት    አሳድጎታል   እንዲያውም  የእንጨት ስራ  በሚሰራበት  ወቅት  ስራውን  ያከናውን የነበረው ለጌታ አንድ  የራሱ  መቀመጫ  ሰርቶለት ፊት ለፊቱ  አስቀምጦት  ዓይን  ዓይኑን  እያየለው እንደነበር ገድሉ ይነግረናል፡፡
     አረጋዊው    ቅዱስ     ዮሴፍ      ከእመቤታችን  በሃዘኗም    በደስታዋው   ጊዜ     አብሯት    በመሆን አገልግሏታል፡፡
    በመፅሐፍ  ቅዱስ  ላይ  ተፅፎ  እንደምናነበው ሙሴ በፈፀመው   ስህተት    (እራሱን   ከእግዚአብሔር  ጋር    አስተካክሎ ‹‹ከዚህ   ድንጋይ     ውሃ እናወጣላችኋለን››   ዘሁ.20፡10-13  በማለቱ)    አርባ  አመት  የደከመበትን     አገልግሎት     ከነአንን     እንደማይወርሳት      እና   እንደሚሞት   ቢነገረውም አገልግሎቱን ግን ቀጠለ፡፡
    እሱ   ያገለግል    የነበረው    ስለ   እግዚአብሔር ፍቅርና  ስለ   እውነት    ነበር   እንጂ   ስለ   ከነአን አልነበረም፡፡ ልክ  እንደሙሴ   ሁሉ   በብሉይ   ኪዳን የነበሩ አባቶች ከሞት  በኋላ  ወደ  ሲዖል  እንደሚወርዱ እያወቁ   በዘመናቸው  ሁሉ እግዚአብሔርን አገልግለው አልፈዋል፡፡ 
    በሐዲስ  ኪዳንም  የመጀመሪያው  ሐዋሪያ  የሆነው አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ   በስደት   ወቅት   ልጁ   ዮሳ ሔሮድስን ከኋላቸው ስለላከባቸው አራት ሰራዊት ጦር  እና  በቤተልሔምና   በአውራጃዋ  ስለተፈፀመው የእናቶች መከራና የህፃናቱ  ሲቃ  አንድም  ሳይቀር በነገራቸው ሰዓት  እመቤታችን    ቅድስት     ድንግል   ማርያም   በከፍተኛ   ደረጃ    በመደንገጧ     ጌታም  የእናቱን ድንጋጤ ተመልክቶ   ‹‹ዮሳ  አመጣጥህ  ዋጋ የሚያሰጥ   ነበር   ነገር  ግን  እናቴን  በማይገባ አስደነገጥካት በል በዳግም  ምፅአት  መጥቼ   ዋጋህን  እስክሰጥህ  ድረስ   ይችን    ድንጋይ   ተንተርሰህ  ለዘመናት  አንቀላፋ››  በማለት  ስለተናገረው   ዮሳ  ከዚያች   ደቂቃ   ጀምሮ  ነፍሱ ከሥጋው ተለይታው ሞተ፡፡
     አረጋዊው ቅዱስ የሴፍ  ይሔን  ሁሉ  በዓይኑ እያየ በቃ  ከዚህ  በኋላ  ልጄን ገሎብኛል  ማገልገል  የለብኝም ሳይል  እና  ሳሳይማረር   ታማኝ    አገልጋይ   መሆኑን አሳይቶናል፡፡
ዮሴፍ ፃድቅ ነበር፡፡ ማቴ.1፡19
     ጻድቅ  ማለት    እውነተኛ    ለእውነት    የቆመ ቅድስና ያለው በመልካም  ሥራው  የተመሰከረለት፣ ከክፉ ስራ  ሁሉ  የራቀ፣  በማንኛውም  ነገር  ነቀፋ የሌለበት ደግና ንፁህ ሰው ማለት ነው፡፡
     ነቢዩ  ሙሴ  በኃላፊነት   ለሚመራው  የእስራኤል ሕዝብ     የሚከተለውን     መመሪያ    ሰጥቶ    ነበር ‹‹የአምላክህን  የእግዚአብሔርን    ቃል   ብትሰማ   ዛሬ ያዘዝኩህን   ትዕዛዙን   ሁሉ    ብታደርግ    ብጠብቅም አምላክህ  እግዚአብሔር  ከምድር አሕዛብ ሁሉ ከፍ  ከፍ ያደርግሃል የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል  ብትሰማ  እነዚህ   በረከቶች   ሁሉ   ይመጡልሃል  ያገኙኅማል፡፡ አንተ በከተማህ ብሩክ ትሆናለህ …..›› ዘዳ.28፡1-7
     የአምላክን    ቃልና      ትዕዛዝ     ለመስማትና ለመጠበቅ  በረከትንም  ለማግኘት  በወቅቱ   የታደለው የእስራኤል  ሕዝብ   ነው፡፡   ዮሴፍም   ከዚህ   ሕዝብ መካከል የተገኘ እስራኤላዊ ፃድቅ ነበር፡፡
     የአረጋዊው  የቅዱስ  ዮሴፍ   ፃድቅነት   በምናኔ፣ በገዳም    በሚደረግ     ተጋድሎ     ሳይሆን   አብሮ በሚኖርበት     ሕብረተሰብ     ውስጥ     በሚያሳየው ደግነትና በነበረው ፍፁምነት ነው፡፡
     አረጋዊው  ቅዱስ  ዮሴፍ   በፈፀመው   ተጋድሎና በሳየው ታማኝነት እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ባዘጋጀው እና  በሚሰጠው     ደስታና    ክብር    የፅድቅ    አክሊል ለመቀናጀት በ114 ዓመቱ  ሐምሌ  26   ቀን   በክብር አርፏል፡፡
‹‹የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት  የከበረ  ነው›› መዝ.115፡6

ጸሎቱና በረከቱ በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን!

ቅዱስ ዮሴፍ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 

የታመነ የከበረ የተመሰገነ ስለሚሆን ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን ዕንወቅ እርሱ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የሚፈጸመውን ምሥጢር አላወቀምና፡፡
አገልጋይ የሆነለት ምሥጢር ምንም እንደሆነ አላወቀም ለእርሱ ከታጨችለት ከድንግል ነቢያት ስለ እርሱ የተናገሩለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ዘር እንዲወለድ አላወቀም በነቢይ እንደተናገረ ሕፃን ያለ አባት ከድንግል እንዲገኝ አላወቀም፡፡ኢሳ 7፡14፣9፡6-7፣ ዮሐ1፡46፡፡
ከንጹሕ ዘር የተፈጠረች ድንግል የእግዚአብሔር ማደርያ እንድትሆን አላወቀም ዘለዓለም መለወጥ የሌለበት ዳግማይ አዳም ክርስቶስ ድንግልና ካላት ገነት እመቤታችን እንዲገኝ አላወቀም፡፡ዘፍ 9፡27፣መኃ 4፡12
ፍጡራንን ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ ያለ ዘር እንዲወለድ አላወቀም በምድራችን ታየ ተብሎ በነቢይ እንደተናገረና ዳግመኛም ምድር ፍሬን ትሰጣለች ተብሎ እንደተናገረ ፡፡ኢሳ 32፡1-2፣ዮሐ1፡4፣ቆላ 1፡15-18፣መኃ2፡12፣መዝ 85፡12
የድንግል ሆድዋ ገፋ ያለዘር የፀነሰች ድንግልን የሆድዋን መግፋት ባየ ጊዜ የዮሴፍ ልቡ አዘነ የንጽሕት እመቤታችንን ምሥጢሯን ፈጽሞ መረመረና በማያውቀው ምሥጢር ጸንሳ ቢያገኛት በጽኑ አሳብ በማውጣት በማውረድ ተያዘ፡፡
ፀንሳ አገኛት በዘር የፀነሰችም መሰለው ከርሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና አንተም እንደምትጠራጠረው አይደለምና ዮሴፍ አትፍራ ብሎ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ እስኪነግረው ድረስ፡፡

ዮሴፍም ይህን በሰማ ጊዜ ለድንግል ሰገደ ንጽሕናዋንም አመነ ነቢዩ ኢሳይያስ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙም አማኑኤል ይባላል ትርጓሜው እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ሆነ ማለት ነው ብሎ የተናገረላት ድንግል እርሷ እንደሆነች ዐወቀ፡፡ማቴ 1፡18-25፣ሉቃ 1፡26-39፣ኢሳ 7፡14፡፡/ሃይማኖተ አበው ዘ ቅዱስ ኤራቅሊስ ምዕራፍ 48 ክፍል 8 ቁጥር 29-35 እንኳን ለፃዲቁ አባታችን ለቅዱስ ዮሴፍ በዓለ እረፍት በሰላም አደረሰን በረከት ረድኤቱ አይለየን አሜን፡፡

ዓርብ 25 ጁላይ 2014

መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት ስሕተት ነውን?


ቅዱስ ዳዊት በግልጥ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ ‹‹ያድናቸውማል›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ ‹‹ያድናቸውማል›› ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ ‹‹ያድናሉ›› እያለ እኛ ‹‹አያድኑም›› ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?

በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ውስጥ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ›› በማለት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን እንደባረከ እናነባለን፡፡ (ዘፍ48.16) በዚህ ጥቅስ ውስጥ መልአክ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ›› እንደሚያድን በግልጽ ተጽፏል፡፡ መላእክት ‹‹ያድናሉ›› ላለማለት እነዚህን ግልጽ ቃላት መላእክት ይጠብቃሉ፤ ይራዳሉ፤ ያግዛሉ በማለት ማድበስበስ ይኖርብን ይሆን? ይህ ሁሉ ዝርዝሩ ሥራቸው ቢሆንም እንደሚድኑም ተጽፏልና ማመን ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ የተናገረውን ቃል እናቶችና አባቶች በስእለታቸው ‹‹ቅዱስ ሚካኤል አድነኝ፤ ቅዱስ ግብርኤል ድረስልኝ›› እያሉ በመድገማቸው የዋሃን ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማያውቁ ነው መባል አለባቸው? ቅዱስ ዳዊትና ቅዱስ ያዕቆብ የመላእክትን አዳኝነት በግልጽ ያወጁት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው ስላልተማሩ ይሆን? ወይስ አንድ ሰባኪ የመላእክትን አዳኝነት ስላስተማረ ‹‹ገድል ጠቃሽ›› በሚል መጥላላት አለበት? ዘማርያኑስ በዚህ መልኩ መዘመራቸው ሊያስወቅሳቸው ይገባ ነበር?

መላእክት የእግዚአብሔር ናቸው፡፡ የፈጠራቸው እርሱ ነው፡፡ የሚፈጽሙትም የእርሱን ፈቃድ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእርሱ መሆናቸውን በሚያሳይ አገላለጥ ‹‹መልአኩ፣ የጌታ መልአክ፣ መላእክቱ›› እያለ ይጠራቸዋል፡፡ ‹‹የጌታ መልአክ በሕልም ታየው›› እንዲል፡፡ (ማቴ1.20) መላእክት ሲያድኑ ፈጣሪ ሥራ አልሠራም ማለት አይደለም፡፡ መላእክት ያለ እርሱ ፈቃድ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ሥራ እንዲሠሩ የሚፈቅድላቸውና የሚያዛቸው እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ እነርሱ የሠሩትን ይዘን ‹‹ፈጣሪ ይህን አደረገ ማለት እንችላለን›› እርሱ አዟቸውና ፈቅዶላቸው እስከሠሩት ድረስ እርሱ ሠራ ማለት ነውና፡፡ የሚቀጥሉት ሦስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች ይህን ሐሳብ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

ለምሳሌ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ጅራፍ እንዲሠሩ አዘዛቸው፡፡ ራሱ ግን ጅራፍ አልሠራም፡፡ ቢሆንም ግን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንደሠራ አድርጎ ‹‹የገመድ ጅራፍ አበጅቶ›› ይላል፡፡ (ዮሐ2.15) ዳግመኛም ኢየሱስ ክርስቶስ ማንንም አላጠመቀም ሐዋርያቱ ግን እንዲያጠምቁ አዟቸዋል፡፡ ያዘዛቸው እርሱ በመሆኑ ‹‹ያጠምቃል እጅግም ደቀመዛሙርት ያደርጋል›› የሚል ወሬ በፈሪሳውያን ዘንድ ተሰምቷል፡፡ ራሱ ግን ማንንም አላጠመቀም ነበር፡፡ (ዮሐ4.1-3) ሌላ ምሳሌ ለመጨመር እነ ሐና እና ቀያፋ ራሳቸው ኢየሱስ ክርስቶስን አልሰቀሉትም፡፡ ነገር ግን ተባባሪዎችና ትእዛዝ ሰጪዎች ስለነበሩ ቅዱስ ጴጥሮሰ ‹‹እናንተ በሰቀላችሁት›› ሲል ሰቃዮች መሆናቸውን ጠቅሶ ወቅሷቸዋል፡፡ (የሐዋ4.10)

በአንጻሩ ደግሞ ሥልጣኑ የፈጣሪ ነው ማለት መላእክት ‹‹ይህን ሠሩ›› አይባልም ማለት አይደለም፡፡ ፈጣሪ በመላእክት ሲሠራ መላእክትን እንደ ቁስ ቆጥሮ ይሠራባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ መላእክት ሕያዋን ናቸው፡፡ የማዘንና የመደሰት ስሜት አላቸው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ንስሐ በሚገባ ኃጢአተኛ ደስ እንደሚላቸው አይጻፍም ነበር፡፡ ስለዚህ መላእክት ደስ እንደሚሰኙ ሁሉ ያዝናሉ ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ ሲያዛቸው በፈቃደኝነት ይታዘዛሉ፡፡ ፈጣሪ በእነርሱ ይሠራል ማለት ያለፈቃዳቸው ይልካቸዋል ማለት አይደለም፡፡ እንደ ሰው ልጅ ነጻነት አላቸው፡፡ ቢሆንም በእርሱ ፈቃድ ደስ ስለሚላቸው ከፈቃዱ ፈቀቅ አይሉም፡፡ ነጻ ፈቃድ ባይኖራቸው ኖሮ ሰይጣን በደለኛ ሆኖ አይገኝም ነበር፡፡ የሰይጣን ወደ ገዛ ፈቃዱ ማዘንበል ለመላእክት የተሰጣቸውን ነጻነት ያሳያል፡፡ ታዲያ ሥራቸውን ወደው የሚሠሩ ሆነው ሳለ ፈጣሪ ልኮአቸው መላእክት ቢያድኑ ‹‹አላዳኑም›› እንዴት እንላለን? ለማዳን ፈቃደኛ ሆነው እስካዳኑ ድረስ ‹‹አድነዋል፣ ያድናሉ›› ማለት የሚገባ አይደለምን?

መላእክት እግዚአብሔር ስለፈቀደላቸው የሠሩትን ሥራ እነርሱ አልሠሩትም ካልን ሰይጣን የፈጸመውን የጥፋት ተግባር ማን ሠራው ልንል ነው? መቼም እግዚአብሔር ሳይፈቅድለት ሰይጣንም ቢሆን ያሰበውን ማከናወን እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ሰይጣን የሠራውን ፈቃጁ አካል እግዚአብሔር ስለሆነ ፈጣሪ ይህን አደረገ እንጂ ሰይጣን ይህን አልሠራውም እንላለንን? እንዲሁም ፈቃጁና አዛዡ ምንም ፈጣሪ ቢሆን ቅዱሳን መላእክት የሠሩትን እንደሠሩት ማመንና መመስከር ይገባል፡፡ ለክፉ ሥራው ሰይጣን ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም ለሥራቸው ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ቂርቆስንና ኢየሉጣን ስላዳነ ‹‹ቅዱስ ገበርኤል አዳናቸው!›› የሚገባ ነው፡፡

በቅዱሳን መላእክት ማዳንና ተራዳኢነት ውስጥ የእግዚአብሔር ሥልጣንና አዛዥነት በረቂቅ አለበት፡፡ እግዚአብሔር ሰዎችን ለማዳን በምንም መንገድ ቢሠራ በዛ ውስጥ የእርሱ ሥልጣንና ሥራ የማይጠረጠር ነው፡፡ መላእክት ያለ ፈጣሪ ትእዛዝና ፈቃድ አንዳች ሊሠሩ አይችሉም፡፡ ፈጣሪ ግን ያለ መላእክት አጋዥነት የፈለገውን የሚሠራ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ፈጣሪ ይህን ሠራ ስንል መላእክትን ላይጨምር ይችላል፡፡ መላእክት ይህን አደረጉ ስንል ግን በምንም ተአምር ከፈጣሪ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ መናፍቃን ‹‹ጌታ፣ እግዚአብሔር ይህን አደረገ›› ብቻ እንድንል የሚፈልጉት ቅዱሳንን ላለማስገባት ነው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ቅዱሳን መላእክትንና ቅዱሳን ሰዎችን ይህን አደረጉ የምንለው እግዚአብሔርን ከማመን ጋር ስለ ቅዱሳን ክብር ለመመስከር ነው፡፡

እሳት በባሕርይው የሚፋጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንጨትና ብረት ግን ብቻቸውን ሳሉ ቢነኳቸው አያቃጥሉም፡፡ ነገር ግን ከእሳት ጋር ከተዋሐዱ /ከጋሉ/ በኋላ ቢነኳቸው ይፋጃሉ፡፡  እሳት የተዋሐደው ብረት የማያቃጥልበት ምንም ሁኔታ የለም፡፡ ካላቃጠለ ወይ እሳት አልተዋሐደውም ወይም ደግሞ እሳቱ ራሱ አያቃጥልም ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም እግዚአብሔር በባሕርይው አዳኝ ነው፡፡ መላእክት አያድኑም ካልን ወይ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር አይደለም ማለት ነው ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ አያድንም እንደማለት ይቆጠርብናል፡፡ ስለዚህ ‹‹መላእክት ያድናሉ›› ስንል የሚያድን እግዚአብሔር ከእነርሱ እንደማይለይ እየመሰከርን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡


የእግዚአብሔር ቸርነት
የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አይለየን!

ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ