ቅዳሜ 19 ጁላይ 2014

ክርስትናና ወጣትነት/ክፍል አራት/


 ካለፈው የቀጠለ /ዓላማ/ በ ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን                    
 ወረት      
አንዳንድ ወጣት ብዙ ነገሮችን መሞከር ደስ የሚለው አለ:: በዓለማዊ ሕይወቱ አንድ ሰሞን ስፖርተኛ ሌላ ሰሞን ደራሲ ሌላ ሰሞን የኮሌጅ ተማሪ ሌላ ወቅት ደግሞ ዳንሰኛ ወዘተ...   ይሆናል::ጠዋት ተነስቶ ሲሮጥ ያዩት ሰዎች ስፖርተኛ ሆነ ብለው ተናግረው ሳይፈጽሙ ሐሳቡን ቀይሮ ደራሲ ለመሆን ፀጉሩን ሲያሳድግ ያገኙታል::ሁለትና ሦስት አንቀጽ የጻፈውን ጽሑፍ  እያሳያቸው አጀማመሬ እንዴት ነው ? ጥሩ ደራሲ ነኝ ሲል ያዳምጡታል።በደራሲነቱ ጥቂት ወራት እንደሰነበተ የተማረ ለመሆን ኮሌጅ ገብቶ ደብተር ጨብጦ አሁን በቃ ቆርጫለሁ ተምሬ ሃገሬን ለማገልገል አስቤአለሁ ይህች ሃገረ የተማረ የሰው ሃይል እጥረት አለባት ማለት ይጀምራል። ብዙም ሳይቆይ ሀገሪቱ የምታድገው በትምህርት ሳይሆን በኢንቨስትመንት ነው በሚል ነጋዴ ለመሆን የአስመጪና ላኪ ፈቃድም ያወጣል።

እንዲህ ዓይነት ወረተኛ ሰው በሃይማኖትም ሁሉን ልሞክር ቢል አይደንቅም። አንድ ሰሞን ፕሮቴስታንት ሆኖ  የሰፈሩን ሰው ሁሉ ካልሰበኩ ፣ ሌላ ሰሞን የጄሆቫ እምነት ተከታይ ሆኖ ኮትና ሱሪ ለብሼ ካልዞርኩ፣ ትንሽ ሲቆይ ደግሞ ሰልሜያለሁ በሚል ጀለቢያ ለብሼ ሶላት ካልሰገድኩ ሊል ይችላል። ይህንን ሁሉ  ሲሞክር ሰንብቶ አሁን ወደ እናት አባቴ ሃይማኖት ተመልሼያለሁ ጥሩ ኦርቶዶክስ እሆናለሁ በሚል ወደ ቤተክርስቲያንም ለመጣ ይችላል ።ቤተክርስቲያን ሲመጣ ነጠላ አጣፍቶ በጠዋት ለቅዳሴ ይገሰግሳል።እንደልማዱ ወረቱ እስኪያበቃ  ይህንንም አይቼዋለሁ ለማለት ጥቂት ጊዜ ትጉህ ይሆናል።እንዲህ ያለ ሰው የእግዚአብሔር ቸርነት ተጨምሮ ጥሩ ጓደኛ አጋጥሞት ወደ ልቡ ካልተመለሰ ወረቱ ሲያበቃ በመጣበት እግሩ ተመልሶ መሄዱ አይቀርም።ከዚህ አንጻር ወረተኛ የሆኑ ወጣቶችን  ፍጥነታቸውን ገትተው በተረጋጋ መንፈስ እንዲጓዙ መምከር የክርስትና ፍጻሜው ሩቅ እንደሆነ ማሳወቅ ተገቢ ነው።

እስኪ እራስህን መርምር ክርስትናህ  ወረታዊ ነው  ወይስ  ገብቶህ እየፈጸምከው ትገኛለህ።ከአጀማመርህ  አንስቶ እስከአሁን ያለህን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለመገምገም ሞክር።ተለዋዋጭ ነው ወይስ ቀጥተኛ?የጸሎት ሕይወትህ ፣ለአገልገሎት ያለህ ትጋት እንዴት  ነው።ዛሬም  እንደጥንቱ ነው ወይስ ተዳክመሀል ?እየተለዋወጠ ያለ ነገር ካለ  ወረት እያጠቃህ መሆኑን አትርሳ።መጠኑ ይለያይ እንጂ  የወረት ክርስትና  በብዙዎች ዘንድ አለ።ይህን አስብና  ከወረት ራቅ።የቀደመ ፍቅርህ ወዴት አለ?እንዳትባል  ከወዲሁ አስብበት/ራእ ዩሐ 2-4/።ክርስትና እስከመቃብር መታመን መሆኑን አትርሳ።ሳትባረድ  እስከመቃብር ለመታመን ወደፈጣሪህ  ጸልይ።ሁልጊዜም እንደጀማሪ ክርስቲያን  በፍሪሃ እግዚአብሔር ፣ በትጋት አገልገል።ይህን ካደረግህ የክርስትና ጉዞ ዓላማ ገብቶሃል ማለት ነው።
  ችግር
ችግሮች ገፍተውት ፣ ከችግሩ ለመላቀቅ ወደቤተ ከርስቲያን የሚመጣ ፣መንፈሳዊ የሚሆንም አለ።ለምሳሌ ትምህርቱን ጨርሶ ሥራ ያጣ ወጣት ሥራ እስኪያገኝ ከቤተሰብ ጥገኝነት ነፃ እስኪወጣ  ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ ይችላል። እንዲህ ያለ ወጣት ችግሩ እስኪፈታለት ማንኛውንም መንፈሳዊ ተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም።በዓውደ ምህረት ፣በሰንበት ትምህርት ቤት ትጉህ ተማሪ ይሆናል።መዝሙር ይዘምራል፣ያስቀድሳል፣ ኪዳን ያደርሳል፣ ሁሉንም በትጋት ያከናውናል። ንስሐ ግባ ቁረብ ቢባል እንኳን ወደ ኋላ አይልም።በዚህ መልኩ  ይቆይና ችግሮቹ ተፈትተው ሥራ ሲያገኝ ጫን ያለ ገቢም ባይሆን ራሱን የሚያስተዳድርበት ገንዘብ መቁጠር ሲጀምር ዓለም ለምኔ እንዳላለ ክርስትና ለምኔ ማለት ይጀምራል።
   እንዲህ ያለው ሰው ክርስትናን የሚሸሸው በመንቀፍ አይደለም። ሰዎች ግምት ውስጥ እንዳያስገቡት በፊት ለፊት ነቀፋም ትችትም የለም።ነገር ግን ራሱን በሥራ ወጣጥሮ ሩጫ እንደሚበዛበት ጊዜ እንደሌለው መናገር ይጀምራል። እሁድ ቀን እንኳን ለቅዳሴ ጊዜ አላገኘሁምና ይቅርታ ይላል። በእርግጥ ሥራ ሲጀምር እንደቀድሞ ላይሆንለት  ጊዜ ይጣበብበት ይሆናል። ነገር ግን ከአንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድምና ለቤተክርስቲያን ጥቂት ጊዜ አይጠፋም። ችግሩ ያለው ባለቤቱ ላይ ነው።ጊዜው ላይ አይደለም። ይህ ወጣት  የምፈልገው ጉዳይ ተስተካክሎልኛል ብሎ ስለሚያስብ ከጓደኞቹ ጋር ይዝናና ይሆናል እንጂ በትርፍ ጊዜው ቤተክርስቲያን አይመጣም።የሚገርመው እንዲህ ያለ ወጣት ከቤተክርስቲያን እንዳይጠፋ ሥራ መጥፋት፣ ችግር መምጣት ያለበት ይመስላል።  

 
ችግር ሲባል ሥራ ማጣት ብቻ አይደለም ።መታመም አንዱ ነው።የታመሙ ወጣቶች  ተስፋ ቆርጠው በመዳንና በመሞት መካከል ሆነው ወደ መንፈሳዊነት ቢመጡ ለጊዜው ፍጹማን ሆነው ይታዩ ይሆናል ።በጠበል ሥፍራ በገዳማት በታላላቅ በዓላት ላይ ነጠላ አጣፍተው እያሸበሸቡ እየዘመሩ ይታያሉ፡፤ ግሸን፣ ላሊበላ፣ ዝቋላ፣ ደብረ ሊባኖስ ፣ ዋልድባ፣ እነዚህንና ሌሎች ታላላቅ ገዳምትን ሁሉ ያዳርሳሉ።እግዚአብሔር ከጭንቀታቸው እስኪገላግላቸው ጠንክረው እየፆሙና እየጸለዩ ይሰነብታሉ።ችግራቸው ገፍቶ በተአምራት ድነው ጤነኛ ሲሆኑ ግን ወዲያውኑ ወደ ኋላ መሸሽ ይጀምራሉ። ባሸበሸቡት እጃቸው ሲደንሱበት፣ በዘመሩበት አንደበት ሲዘፍኑበት ይገኛሉ። ትናንት ያስቀደሱባቸው ፣የተጠመቁባቸውን አድባራትና ገዳማት በዕለት ሳይሆን በወርና በዓመትም መሳለም ያቆማሉ።ዓላማው ጊዜያዊ ሲሆን የሆነና  ችግሬ ይፈታ ብቻ ብሎ የሚቀርብ ወጣት መጨረሻው እንዲህ ይሆናል።ምንም እንኳን ለጊዜው የቀረበበት ምክንያት ችግሩ ቢሆንም  ልቡ ተሰብሮ መንፈሳዊ የሆነና ስለመንግሥተ ሰማያት ማሰብ የጀመረ  ወጣት ግን ጥቂት ገንዘብ የሚያገኝበት ሥራ አይደለም በጣም ብዙ ሀብት በእጁ ቢገባ እንኳን ከእግዚአብሔር ቤት አይርቅም።
የውጭ ፕሮሰስ ጀምረው ቪዛው እጃቸው እስኪገባ ላገኙት ታቦት፣ ለገጠማቸው ቤተክርስቲያን የሚሳሉ ወጣቶች ጥቂቶች አይደሉም።ቪዛው እጃቸው የገባ ዕለት ሻማ አብርተው እልል ይላሉ። ወደ አየር መንገድ እስኪሸኙ ካሰቡበት ሀገር  ገብተው  ቁርጣቸውን እስኪያውቁ ከቦርሳቸው ጸሎት መጽሐፍ አይለይም።ሁሉም አልፎ የባሕር ማዶውን ኑሮ ሲጀምሩ ግን ክርስትናቸው የስንፍና ጥላ ያጠላበታል። ከመንፈሳዊነት ይልቅ የሀገር ቤቶች ዘፋኞች በሚያቀርቧቸው የመዝናኛ ዝግጅት ላይ መታደምን መዝናናትን ይመርጣሉ። ሁሌ ጭፈራ ሁሌ አስረሽ ምችው ይሆናል።
አንተም እንዲህ እንዳትሆን ራስህን ጠይቅ።ተቸግረህ ተጨንቀህ  የነበረህን መንፈሳዊ ጥንካሬ ይዘህ  ለሁል ጊዜውም ቀጥል።ከአበው አንዱ የሆነው አባታችን ያዕቆብ እንዲህ ይላል”አባቶቼ አብርምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር ፣ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፣ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፣እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ያባርክ።”/ዘፍ48-15/ይህ ትናንትን  ካልዘነጋ  መንፈሳዊ ሰው የሚወጣ የእምነት ቃል ነው።አንተም እንደዚሁ ስለትናንተና  ጉዞህ አስብ።የተደረገለህን ፈጽመህ ላለመርሳት ሞክር።የኤርትራ  ባህርን ያሻገረ ፣ከፈራኦን እጅ ያዳነ ፈጣሪ መረሳት የለበትም።ሁል ጊዜም ችግርህን መከራህን በእሳትና በውሃ መካከል ያለፍክበትን ዘመን አትርሳ።ያን ጊዜህ ጉዞህ ዓላማ ያለው መንፈሳው ጉዞ ይሆናል።
እልኽ 
መናፍቃን ተፈታትነውት፣የአንተ ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ መቼ ይሰበክባታል ብለውት ተበሳጭቶ የሚመጣም ወጣትአለ። መናፍቃኑ ማርያም ታማልዳለች ብለህ ታምናለህ እስኪ ካመንህ መልሱን ንገረን የት ላይ ነው የተጻፈው ብለው ሲያዋክቡት ለጊዜው ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ  ያጣል።መልስ በማጣቱ ተቆጥቶ ወደቤተ ክርስቲያን ይመጣል።መናፍቃንንለማንበርከክ አፋቸውን  ለማስያዝ ወደ ቤተክርስቲያን  ይቀርባል።ሰባኪው ወጥቶ ሲሰብክ ስለእመቤታችን አማላጅነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሶ ካስተማረ ጥቅሱን በጥንቃቄ ይይዛል።የሚይዘው ሊማርበት ሳይሆን መናፍቃንን ሊከራከርበት ነው።በዚህ ሁኔታ የተወኑ ጥቅሶች ከሰበሰበ በኋላ በየመንገዱ እየዞረ መናፍቃን አዳኝ ተከራካሪ ይሆናል። እንዲህ ያለ ወጣት ለድኅነት ስለማይማር ወደ ቤተ ክርስትያንም የሚመጣው ለክርክር  ብቻ ስለሆነ መንፈሳዊነት ፆሙ ፣ጸሎቱ፣ ንስሐው፣ቁርባኑ ፈጽሞ ላይታሰበው ይችላል።ለእርሱ ሃይማኖት ማለት ክርክር ማለት ነው።እልኩን እስካልተወጣ እረፍት አይኖረውም።
 መናፍቃንን ለመርታት በእነርሱ ውስጥ ያለውን ክፉ መንፈስ ለማሸነፍ መጀመሪያ በበቂ ሁኔታ መማር ሕይወትን ማስተካከል መንፈሳዊ መሆን ያስፈልጋል።”መጋደላችን  ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም።ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር  ከዚህም ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።ስለዚህም በክፉው ቀን  ለመቃወም ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። ድል እንድትነሱ በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ኤፌ 6-12 ይላል። ክርክሩ ከሰዎች ጋር አይደለምና እነርሱ ጥግ አድርጎ ከሚመጣ ክፉ መንፈስ ጋር ነው።ይህንን ክፉ መንፈስ ድል ለመንሳት ደግሞ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊነት ያስፈልጋል። ሠለስቱ ምእት አርዮስን ለማውገዝ በኒቂያ ሲሰበሰቡ ከሁሉ በፊት ሱባኤ ገብተው ነበር።አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዘግተው መስከረም ሃያ አንድ ቀን ነው ከሱባኤ ወጥተው ድል የነሱት።በመንፈሳዊነ ኃይል ስለቀረቡ አሪዎስ ለጠየቃቸው ጥያቄቆች በቂ መልስ ሰጥተው የቤተክርስቲያኒቱን ክብር አስጠብቀው ጉባኤውን በድል አጣናቀዋል።አንተም በየመንገዱ መናፍቃንን  ከመከራከርህ በፊት ራስህን ቀይር። ዓላማውህ ክርክር ሳይሆን ገነት መንግሥተ ሰማያት ይሁን።ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ።
አንድ ወጣት ትዝ ይለኛል ቤተክርስቲያን ሲመጣ በመናፍቃን ምክንያት ነው።ኋላ ጥቂት ጊዜ ተማረና ክርክር ጀመረ። መናፍቃንን እየተከታተለ መከራከሩን ቀጠለ። አባቶች እንዲተው መከሩት መጀመሪያ ተቀምጠህ ተማር አሉት።አልሰማቸውም በዚህ መልኩ ስድስት ሰባት ወር ያህል ሲከራከር ከቆየ በኋላ ከእነርሱ ተከራክሮ ሲመለስ ተደበላልቆበት የተመረዘ ሀሳብ ይዞ ይመጣ ጀመር።ግማሽ የፕሮቴስታንት፣ግማሽ የኦርቶዶክስ ሃሳብ ይዞ መጓዝ ጀመረ።ጓደኞቹ ሲያነጋግሩት አንዳንድ ጊዜ የሚናገረው ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚጋጭ ስለሆነ መግባባት አቃታቸው።ተው ቢሉትም ክርክር ስለሚወድ ከእነርሱም ጋር መከራከር ጀመረ።ይህ ልጅ እያለ እያለ ተደባልቆበት ጭንቅላቱ እስከመበላሸት ደርሶ ወደ አንድ የጠበል ቦታ ተወሰደ።ሁሉን መደባለቅ ሳይጸኑ ሳይበረቱ ለክርክር መዘጋጀት መጨረሻው አስቸጋሪ ነው።
    መናፍቃንን በማሰብ መጥተህ ከሆነ  ወደፊት የነርሱን ነገር ብቻ በማሰብ ላለመድከም ሞክር።ከሁሉ በፊት ራስህን አድን።የጠራህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው እንዳለ አትርሳ።ሌሎችን ለማዳን መጀመሪያ አንተ ብርቱ ሁን።መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ ለሌሎች መልስ ለማግኘት ሳይሆን ለአንተ ሕይወት የሚጠቅመውን ለመውሰድ ይሁን።የእልኸኝነት ጉዞህን በመንፈሳዊነት ተካው።
         ይቆየን



ዓርብ 18 ጁላይ 2014

ውዳሴ አምላክ ዘቀዳም


የቅዱስ መልአክ ጸሎት
የምትጠብቀኝ መልአክ ሆይ ዛሬ ወደ ቅዱስ ቁርባን የምቀርብ ነኝና ቁርባንም ስለ ክብሩ ብዛት የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ ሥራት ነውና እጅግ እፋራዋለሁ ስለዚህ አንተ ተከተለኝ ጌታዬ የሚገባ ልመና እንድለምነው አንተ ጌታዬን እንዴት እቀበልሃለሁ ይሆን እንዳልል ለልቤ መንፈሳዊ እውቀትን አሳይልኝ፡፡የኔ ልብ ካንተ በዚህ ታቦት ዙርያ ከሚቆሙት ከባልንጀሮችህ ልብ ጋራ እንዲሆን የልብ ትሕትና የልብ ፍቅር አስተምረኝ፡፡የምትረዱ ቅዱሳን ሁሉ ተከተሉኝ ጠብቁኝ፡፡
ዘቀዳም
ውዳሴ አምላክ
በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አምናለሁ፡፡መግደልና ማዳን በሚቻለው አመንሁ ሞትና ሕይወት በእጁ ባለ አመንሁ መንፈሳዊውንም ሕይወት በሚሰጠው አምናለሁ፡፡በኪሩቤል ላይ በተቀመጠው አምናለሁ፡፡ምድርን ባያት ጊዜ እስከ መሠረቷ እንድትንቀጠቀጥ በሚያደርጋት አምናለሁ፡፡
አዳምን ልጆቹንም በምሳሌው በፈጠራቸው አምናለሁ፡፡አዳምና ልጆቹንም ለማዳን በመምጣቱ አምናለሁ ከንጽሕት ድንግል ከእመቤታችን ሰው በመሆኑ አምናለሁ፡፡ እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ ባለው አምናለሁ፡፡
የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ በኔ ያመነ አይሞትም ቢሞትም እኔ አሥነሳዋለሁ ባለው አምናለሁ ለፍጥረቱ ሕይወትን በሰጠ አምናለሁ እኔ በአብ እኖራለሁ አብም በኔ ይኖራል ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› ባለው አምናለሁ ኃጥአንን ወደ ንስሓ ይጠራ ዘንድ በመጣው ለፍጥረቱም ኃይልና ሥርየትን በሰጠው አምናለሁ፡፡
በጽሩይ ልቡና የሚለምኑትን በርኅራኄው ብዛት በሚቀበላቸው አምናለሁ፡፡ሳይሣሣ በሚሰጥ አምናለሁ ሥጋ ያለውን ሁሉ ልመና ሰምቶ ተስፋ በማያስቆርጥ አምናለሁ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለኝ ፡፡ ይቅር ትለኝ ዘንድ ይቅርታህን አያለሁና ያለ አንተ ይቅር ባይ ባይኖር ጌታዬ ሆይ የቀኝ እጅህ ፍጥረት ነኝና ይቅር በለኝ በደለኛ ኃጥእ የነበርሁ እኔ ላገለግልህ መጥቻለሁና ይቅርታህና ርኅራኄህ የበዛ ፈጣሪ ይቅር በለኝ ፡፡ በፊትህ የበደልሁ እኔ በፊትህ ወድቄ አለሁና በጎነትህ የሰፋ ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ የተጠመቁ ክርስቲያንንም ሁሉ ይቅር በላቸው፡፡
ጌታዬ ሆይ በርኅራኄህ ብዛት ይቅር በለኝ፡፡ጌታዬ ሆይ በቸርነትህም ብዛት ይቅር በለኝ፡፡
ለኃጢአቴ ሥርየት ስለ ሠራህልኝ ጥምቀቴ  ይቅር በለኝ፡፡ ኃጢአታችን  ሊሠረይበት እንበላው ዘንድ ስለ ሰጠኸን ስለ አምላካዊ ሥጋህ ይቅር በለኝ፡፡የዘላለም መድኃኒትና ይቅርታን ስለ ሰጠህባት ስለ ሐዲሲቱ ሕግ አቤቱ እኔን ባርያህን ይቅር በለኝ፡፡
ጌታዬ ሆይ ወደ ተወደደ ልጅዋ ይሰማል እንጂ ልመናዋ በማይነቀፍ ይቅር ባይ አማላጅ በምትሆን በእመቤታችን በአማላጃችን ይቅር በለኝ አቤቱ ጌታዬ ሆይ ስለ ኃጢአቴ ብዛት ይህን ካንተ ከመቀበል ምንም የበቃሁ ባልሆን ይቅር በለኝ፡፡የኃጢአቴንም ብዛት አትይ ያለ ንስሓ ኃጢአት የሚያስተሠርይ የለምና፡፡
የኃጢአቴን እድፍ ከይቅርታህ ብዛት ጋራ የምታጽብ አንተ ስለሆንክ፡፡ለጋስ ሆይ ቸር ሆይ ይቅር በለኝ፡፡ሰማይ ስንኳ በአንተ ዘንድ ንጹህ አይደለምና የመላእክት ጭፍሮችም በአንተ ዘንድ ንጹሐን አይደሉም፡፡ንጹሐን ባይሆኑ ከእርሳቸው ወገን ከመዓርጋቸው የተዋረዱ አሉና ስለዚህ የፍጥረት ጌታ ሆይ በአንተ ዘንድ ንጹሕ የለምና  ይቅር በለኝ እላለሁ፡፡
ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ ወራቴ በከንቱ አልቋልና ዘመኔም በከንቱ ተፈጽሟልና ወደ ሌላም ዘመን እንድመለስ ተስፋ የለኝም፡፡
ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ ፡፡በዕዳ ተይዤ አለሁና ነፍሴን ከኃጢአት ማሰሪያ የማስፈታበት የበጎ ሥራ ገንዘብ የለኝምና ክፉ ሥራዬም በዝቷልና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡
እነሆ መከር ደርሷልና አጫጆችም ከራስጌዬ ቁመዋልና  ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡የወይን መቁረጫው ጊዜው ደርሷልና ወይኑ ግን ጮርቃ ነው አይረባኝምና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡እነሆ በማያፈራው ዕንጨት ሁሉ ምሳር ተቃጥቷል ክፉ ዕንጨት የተባለም አንተን የማገለግልበት በጎ ሥራ የሌለኝ እኔ ነኝና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡
እኔ ቸል ስል ሞት ደርሶብኛልና ጌታዬ ሆይ እዘንልኝ፡፡ለመንገዴ ስንቅ የለኝምና መንገዴም እጅግ የምታደክም ናትና ምክንያትም ምላሽም የለኝም ጌታዬ ሆይ ራራልኝ፡፡መልእክተኛ ወደኔ በመጣ ጊዜ እንዳያስቸኩለኝ ከዚህ ዓለም ለመሄድ የበቃሁ አይደለሁምና በሞት ስጨነቅ መንገድም የሚገኘኝን  አላውቅምና ጌታዬ ሆዬ እኔን ግን ያንተን ረዳትነት ተስፋ አደርጋለሁ ያለ ይቅርታህም ተስፋ የለኝም ጌታዬ ሆይ ከርኅራኄህ አታሳፍረኝ በድሎ ወደ አንተ በንስሐ የተመለሰውን አታሳፍረውምና ከመሓሪነትህና ከስጦታህ አታሳፍረኝ ከበዛች ለጋሥነትህም፡፡
ጌታዬ ሆይ ከመመካት አድነኝ ከኩራት አድነኝ ከትዕቢት አድነኝ ልቡናን ከማሳደግ ራስንም ከፍ ከፍ ከማድረግ ከቅናትና ከቂም ከሐሜትም ከባልንጀራም መፍረድ አድነኝ፡፡
 አቤቱ ጌታዬ ሆይ ከታናሹም ከታላቁም ኃጢአት ሰይጣን ከሚያሰራውም  ሥራ ሁሉ አድነኝ፡፡ሥጋንም ደስ ከማሰኘት አድነኝ ፡፡ከጉዳትም አድነን፡፡ አቤቱ ከዳተኛ ወንጀለኛ ከሚሆን አምላካዊ ፍቅርንም ከሚጠላ ከባላጋራዬ ከዲያቢሎስ እጅ አድነኝ፡፡ጠላቴንም በእኔ አታሰናብተው ድል መንሣትንም አትስጠው ድል በነሣ ጊዜ በእርሱ ኃይል ድል እንደነሳኝ አድርጎ እንዳመካ ጌታዬ ሆይ በመዓልት በሌሊትም በጊዜው በየሰዓቱም ሁሉ ጠብቀኝ ከክፉም ከርኩስም ሕሊና ለሚያዋርዱና እንደ እሳት ከሚያቃጥሉም ተጠብቄ እንድኖር አድርገህ ትእግሥትን ስጠኝ በቦታዬም እንድኖር አድርገኝ ሌባ እንዳይሰርቀኝ ከቦታዬም እንዳያናውጠኝ ገንዘቡ ጠፍቶበት ከወንድሞቹ እንደተለየ እንደ ባዕድ እንዳያደርገኝ በጠላቶቼ ፊት አትግለጠኝ እንዳይስቁብኝና እንዳይዘባበቱብኝ የተሠወረ ኃጢአቴንም እንዳይገልጹብኝ በቦታዬ አጽናኝ እንጂ መልካም ፍሬንም እንደምታፈራ እንደ ሠሌን ሥር ጽናት በልቡና ጽናትና በነፍስ ዝምታ በቦታዬ ትከለኝ፡፡
አቤቱ ጌታዬ ሆይ የነፍሴን ነገር እያሰብኩ በኃጢአቴ አለቅስ ዘንድ ልቡናዬ እንዳይታወክ ነፍሴንም በመውጣት በመግባት ካንዱ ወደ አንዱ መዞርን እንዳታደርግ ይህም የሰይጣን ጦርነት ነው ዘመኔም በሥራ ፈትነትና በዙረት እንዳይፈጸም የዲያብሎስንም ኃይል ከሃሊነት ባለው ሥልጣንህ አጥፋው እኔ ባርያህ በሥራዬ ሁሉ ደካማ ነኝና አባትና እናት እንደሌሉት ሕፃን በየጊዜው ሁሉ ወደ አንተ አንጋጥጣለሁ ባል እንደሌላት እንደተዋረደችም ሴት ደዌውም እንደ ጸናችበት ድውይ በቁስል ላይ ቁስል እንደ ተጨመረበት የሚፈውሰውንም ባለመድኃኒት እንደሚሻ፡፡
መዝሙረ ዳዊት 85
1 አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና።
2 ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው።
3 አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ።
4 የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።
5 አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና።
6 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ።
7 ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ።
8 አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም።
9 ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ
10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።
11 አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።
12 አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ
13 ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና።
14 አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት በፊታቸውም አላደረጉህም።
15 አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ
16 ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
17 ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።


ክርስትናና ወጣትነት /ክፍል ሦስት/

በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን
ዓላማ
  ካለፈው የቀጠለ 
         አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን በከመ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት ከማሁ ያስተጋብእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት ወበኢየሩሳሌም አግዓዚት እንተ በሰማያት። እናንተ የክርስቲያን ወገኖች ዛሬ በዚህች ዕለት እንደተሰበሰባችሁ እንደዚህ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮንና በሰማይ ባለች  ነጻ በምታወጣ በኢየሩሳሌም ይሰብስባችሁ።”/ቅዳሴ ማርያም ቁ.156/ይላል። በዚህች ዕለት ያለው ቀድሶ ያቆረበበትን ነው ። በዚህች ዕለት በቤተክርስቲያን እንደተሰበሰባችሁ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮን ይሰብስባችሁ ከተፈጥሮተ እደ ሰብእ ነፃ በምትሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊትም ይሰብስባችሁ ሲለን ነው።
            ይህ አባት በመቀጠል ስለመንግሥተ ሰማያት ሲተነትን  “ይህን የእመቤታችንን የምስጋና ቃል እንደሰማችሁ የሕጻናትን ምስጋና ያሰማችሁ።"ይላል። እነዚህ ሕጻናት በዘመነ ሔሮድስ መከራ ተቀብለው ያለፉ ናቸው። እነርሱ ከደረሱበት ማዕረግ ያድርሳችሁ፣ በመከራ ጸንታችሁ እነርሱ ከገቡበት ያግባችሁ ሲል ነው።"ወማሕሌተ ዘመላእክት ዘያጠልል አዕፅምተ እምብዝኃ ጣዕሙ ፈድፋደ።"  የመላእክትነት ምስጋና ያሰማችሁ ከደስታው ብዛት የተነሳ አጥንትን የሚያለመልም በተፈጥሮ ገንዘብ አድርገውት የሚኖሩትን የመላዕክትን  ምስጋና ያሰማችሁ ሲለን ነው። 
           "ያብእክሙ ኀበ ተተክሉ ደባትር ዘነደ እሳት። ሰባት የእሳት መጋረጃ ካለበት።"ነደ እሳት ጌታ የሚያወርሰው ሀብት ካለበት መንግስተ ሰማያት ያግባችሁ።"ኀበ ሀሎ ሊቀ ካህናት።ህየ ሀሎ መልክአ ገጹ ሥዑል፣አክሊል ንጹሕ፣ ወአልባስ ብሩህ ዘኢተኬነዎ እደ እጏለ  እመ ሕያው።አላ ዘእምላዕሉ አንትሙ።የካህናት አለቃ ወዳለበት ያግባችሁ፣የተሳለ የፊቱ መልክ ከዚያ አለ።ንጹሕ አክሊልና ብርህ ልብስ ከዚያ አለ።እርሱም ከላይ የተገኘ ነው የሰው እጅ ያልተጠበበት ነው።"አክሊል ያለው መንግሥተ ሰማያት። አልባስ ያለው እግዚአብሄር  ለወዳጆቹ ለምእመናን የሚያወርሰው ክብር ነው።ለምእመናን የሚያወርሰው ክብር ካለበት  ከመንግሥተ ሰማያት ያግባችሁ።"ያብእክሙ ኀበ ሀለዉ ማኀበረ ነቢያት ቅዱሳን።" ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ ያላቸው የተመረጡ የነቢያት ወገኖች ካሉበት። "ወማኀበረ ሐዋርያት ሰባኪያን "ቃላቸው ወደ ዓለም ሁሉ ወጣ ነገራቸውም እስከ ምድረ ዳርቻ ተሰማ ተብሎ የተነገረላቸው የሐዋርያት ወገን ካሉበት፣ ያግባችሁ። "ወማኀበረ ሰማዕት መዋዕያን።ድል የነሱ የሰማዕታትም ማኅበር ካሉበት ያግባችሁ።ወማኅበረ ጻድቃን ቡሩካን ።ቡሩካን የጻድቃን ወገኖች ካሉበት።ወማኅበረ መላእክት ትጉኃን።ትጉኃን የሚሆኑ የመላእክት አንድነት ካለበት ያግባችሁ።ወማኅበረ ደናግል ወመነኮሳት ፍጹማን ።ፍጹማን የሚሆኑ የመነኮሳት የደናግል ወገኖች ካሉበት ያግባችሁ።ወምስለ ኩሉ ፍጻሜ ማኀበራ ለቅድስት አሐቲ እንተ ላዕለ ኩሉ ቤተክርስቲያን።ከሁሉ በላይ ከሆነች ከአንዲት ቅድስት ቤት ክርስቲያን አንድነትዋ ሁሉ ጋር ያግባችሁ።"ከምእመናነ አሕዝብ በላይ የምትሆን የምእመናን ፍጹም አንድነቷ ካለበት ያግባችሁ። "ወምስሌሆሙ ታቦት ዘዶር እንተ ይእቲ እግዝእትነ ማርያም።ከእነርሱም ጋር ታቦት ዘዶር ወዳለችበት ይህችውም እመቤታችን ናት።"ይላል።የእመቤታችን ምሳሌ የምትሆን ታቦት ዘዶር ካለችበት ከመንግሥተ ሰማያት ያግባችሁ። አንድም የጌታ ማደሪያ የምትሆን የብርሃን ታቦት እመቤታችን ካለችበት ያግባችሁ ሲለን ነው።አባ ሕርያቆስ በሥርዓተ ቅዳሴ ለመሳተፍ የተሰበሰቡ ካህናትንና ምዕምናንን ባንድነት ከላይ ባየነው መልኩ  ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃን ያብቃችሁ ይላል። ምክንያቱም የማስቀደሱም የመቀደሱም፣የመማሩም የማስተማሩም፣ የመዘመር የማዘመሩም፣ የሁሉም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ዓላማ ለመንግሥተ ሰማያት መብቃት ስለሆነ ያንን ሲያዝገነዝበን ነው።
 "
           ቅዱስ አትናቴዎሰም በቅዳሴ ድርሰቱ" ገደል ጉጻጉጽ ቀና ያይደለ ጠማማ የሆነ አገር ከዚህ ያለን አይደለም ነቢያትና ሐዋርያት አስቀድመው የደረሱበት በልዕልና ያለ ነው እንጂ። ለእኛ ከዚሕ በአሸዋ  የተሠራ ነፋሳት የሚነፍሱበት ፈሳሾች የሚገፉት ቤት ያለን አይደለም።በላይ ያለች ነጻ የምታወጣ ኢየሩሳሌም ናት እንጂ። አስቀድመው የጳጳሳት አለቆች፣ ጳጳሳት ፣ኤጴስ ቆጶሳት፣ቀሳውስትና ዲያቆናትም የገቡባት ናት እንጂ። እኚህ እንደኛ ሥጋን የለበሱ ሲሆኑ ባነዋወራቸው መላእክትን መሰሉ።ሰውነታቸውን አነጹ ልብሳቸውንም ነጭ  አደረጉ። የሥጋቸውንም አዳራሽነት አላሳደፉም ስማቸው በበጉ ደም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጻፈ "/ቅዳሴ አትናቴዎስ ቁ.49/ይለናል።በምድራዊ ኑሮ ላይ ብቻ ተደግፎ ሕሊናችን ከመንግሥተ ሰማያት እንዳይርቅ መኖሪያችን ይህ አይደለም ሀገራችን በሰማይ ነው እያለ ይመክረናል።
        ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ነገር ሲጽፍ “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት።ከዚያም ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እሱን  እንጠብቃለን ።”/ ፊሊጲ 3-20 /ብሏል።ሀገራችን በሰማይ መሆኑን ተረድተን በሩቅ የምናያት መንግሥት ሰማያትን ተስፋ እያደረግን  ብንጓዝ በምድር ላይ ያለ ክብር፣ ዝና ፣ሀብት፣ብልጽግና ፣ሁሉም ከጀመርነው ጉዞ አያስቀሩንም።
         ቅዱስ ጳውሎስ” መኑ የኀድገነ ፍቁሮ ለክርስቶስ።ከክርስቶሰ ፍቅር  የሚለየን ማነው? የክርስቶስን ፍቅር ማን ያስተወናል? ሕማም ነውን? መከራ ነውን? ስደት ነውን ?ረኃብ ነውን ?መራቆት ነውን ?ሾተል ነውን? ጭንቅ ነውን?ይለናል/ ሮሜ 8-35/። መንፈሳዊ ሰው መከራ ቢፈራረቅበት ችግር እንደ ዶፍ ዝናብ ቢወርድበት ከክርስቶስ ፍቅር አይለየውም በመከራ ውስጥ ሁል  ጊዜ ክርስቶስ በፍርድ ቀን የሚያወርሰውን መንግሥተ ሰማያት ያስባል። በዚህም ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ሲጠራው ለአምላኩ ይታመናል።ሐዋርያው "የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል?እንዴትስ ደጅ ይጠናል? የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን ትዕግሥታችን ይታወቃል። እሱን ተስፋ  አድርገን በእርሱ እንደጸናን መጠን ይለናል/ ሮሜ 8-25/። ክርስቲያን የማይታየውን ዓይን ያላያት ጆሮ ያልሰማት እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ ያዘጋጃትን  መንግሥተ ሰማያትን ተስፋ ማድረጉ ብፁዕ ያሰኘዋል። የማይታየውን ተስፋ አድርጎ በሚታየው ዓለም ላይ የሥጋ ምቾት የዓይን አምሮት መናቁ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ አለማለቱ ብፁዕ ያሰኘዋል።
             አንጢላሪዮስ የተባለ ሰው ባለፀጋ ነበር ነዳይ መጥቶ ከደጁ ይቆማል። ይህን ደሃ ለማባረር አስቦ ድንጋይ ቢያጣ ዳቦ ወርውሮ መታው።ደሃው ርቦት ስለነበር በደሙ የተለወሰውን የተፈነከተበትን ዳቦ አንስቶ ይዞ ይሄዳል።አንጢላሪዮስ በዚያን ሌሊት ራዕይ ተመለከተ። መላእክተ ጽልመት /የጨለማ መላእክት/ ነፍሱን ከሥጋው ለይተው ይዘውት ሲሄዱ ቅዱሳን መላእክት እያዘኑ ተከተሏቸው።የጨለማ መላእክትም ከዚህ ምን  አላችሁ ቢሏቸው ትላንትና የመጸወተውስ ብለው ቅዱሳን መላእክት መለሱ።በዳቦው መታው እንጂ መቼ መጸወተ ተብሎ ደሃው እንዲመሰክር ተጠራ። ያ ነዳይም ትላንትና ያጠገበኝ ይህ ባለ ጸጋ ነው ከረሃቡ ጽናት የተነሳ የፈሰሰኝ ደም አልታወቀኝም ብሎ መስክሮለታል። አንጢላሪዮስ ይህን ራዕይ አይቶ ሲነቃ ምጽዋት ለካ እንዲህ ያጸድቃል ብሎ ያለውን ሁሉ መመፅወት ጀመረ።ራቱን ሳያስቀር መጸወተ።ከዚህ በኋላ ነዳያን ምጽዋት እያሉ ሲያስጀግሩት ጎበዝ ባሪያ አለ ብላችሁ ሽጡኝና ተካፈሉኝ አላቸው።ለሠላሳ ብር ሸጠውት ተካፍለዋል። የመንግስተ ሰማያት ነገር ሲገባው የሰው ልጅ እንዲህ ይሆናል።ሁሉን  ይተዋል ይህን ዓለም እንደ ጉድፍ ይቆጥረዋል።
            የወጣትነታችን  ሕይወት የተባረከ አገልግሎታችንም የሰመረ እንዲሆን  ልንጓዝበት የሚገባን መንገድ ይህ ነው። ልባችንን በመንገዳችን አድርገን ስለመንግሥተ ሰማያት ማሰብ ይገባናል።ልጅ ሳለን እንደ ልጅ አስበን ይሆናል። ዛሬ ግን በማስተዋል መጓዝ ይጠበቅብናል።እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅድስት አርሴማ ፣በወጣትነት እድሜ ሰማያዊውን ክብር ከማሰብ ጋር የክርስትናኝ ሕይወትን መኖር ይኖርብናል።ይህን ሁሉ የሚያደርገው በውስጣችን ያለ ዓላማ ስለሆነ ጉዞአችን በዓላማ ይሁን።
            አንድ የማውቀው ወጣት ትዝ ይለኛል።ቤተ ክርስቲያን በመጣበት ዓመት ስድስት ወር ሳይሆነው ሁሉንም መሆን ተመኘ ሰባኪ ሲመለከት ሰባኪ፣ ዘማሪ ሲያይ ዘማሪ፣ዲያቆን ሲያይ ዲያቆን፣ባህታዊያን ሲያይ ባህታዊ፣ ለመሆን ያልሞከረው የለም በየዕለቱ በየሳምንቱ ሃሳቡን ይቀያይራል።ካሴት ላወጣ ነው፣ ካህናት ማሰልጠኛ ገብቼ ኮርስ ወስጄ ጎበዝ ሰባኪ ልሆን ነው፣ ገዳም መግባት አስቤያለሁ፣ ይላል።እንዲህ ሁሉንም እየተመኘ ለአንድ ዓመት ቆየ።ከዚያ ሁሉም ስላልሆነለት ተበሳጭቶ ከቤተክርስቲያን ተለየ፡ ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከተለየም በኋላ ነጋዴ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ሯጭ የመሆን ሙከራ ያደርግ ስለነበር የሰፈር ጓደኞቹ መቀለጃ ሆነ።  ' ይህ ወጣት መጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ለክብር ለዝና ታዋቂ ለመሆን ቢሆንም ጥቂት አየቆየ ሲሄድ ቢበስል መልካም ነበር። ነገር ግን ነገሮችን ሳያገናዝብ በዚያው በመጣበት ሐሳብ እንደጸና ለዝናና ለክብር ብቻ እንደሮጠ ከቤተክርስቲያን ተለየ።
                        ትክክለኛ ዓላማ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ከተረዳን። በክርስትና ጉዞ ወጣቱ ከመስመር የሚወጣባቸውን የስህተት ዓላማዎች ጊዜያዊ የስሜት ጉዞዎች የትኞቹ እንደሆኑ ቀጥለን እንመለከታለን።
    ዝና
         ይህ ብዙ ጊዜ የወጣትነት ሕይወት ከትክክለኛው ዓላማ ውጭ እንዲሆን የሚደረግ ነው።መታወቅ መደነቅ አንቱ መባል በመፈለግ  በዕንባ የጀመሩትን መንፈሳዊ ጉዞ ለዝና በመሮጥ ብቻ የሚፈጽሙ ጥቂቶች አይደሉም።ዝነኝነትን ጊዜያዊ ዓላማው ያደረገ ሰው በቤተክርስቲያን ሌትና ቀን ሲወጣና ሲወርድ ሲለፋ ሊታይ ይችላል። ድካሙ ግን ከእግዚአብሔር ሰማያዊ ወጋን ለመቀበል ሳይሆን በምድር ላይ አንቱ ለመባል ነው። ፈሪሳዊያን ይህ አይነቱ ችግር ነበረባቸው።በየማዕዘኑ በመጸለይ፣ ሰውነታቸውን በጨው ታጥበው በመውጣት ጾመኛ በመምሰል፣ በልብሳቸው ቃለ እግዚአብሔርን ጽፈው በመዞር፣ ከእነርሱ በላይ መንፈሳዊ እንደሌለ ከእነርሱ በላይ ቀናኢ እንደሌለ ያስቡ ነበር። ጌታችን ማስተማር ሲጀምር ይህንን ለሰው ታይታ የሚደረግ የፈሪሳዊያንን ጉዞ ነቅፎታል።በምትጸልዩበትም ጊዜ እንደግብዞች አትሁኑ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በየሙክራቡና በየአደባባዩ መዓዘን መቆምንና መጸለይን ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን አጡ።/ ማቴ 6-5 /ብሏቸዋል።ዋጋቸውን አጡ የሚለን በምድር ላይ አቦ አቦ መባልን ስለፈለጉ ሰማያዊ ዋጋን አጡ ሲለን ነው።በሌላ በኩል በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ እነርሱ እንደ ጾሙ ሰው ያውቅላቸው ዘንድ ይጠወልጋሉና። ግንባራቸውንም ይቋጥራሉና። መልካቸውንም ይለውጣሉና። እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀበሉ ይለናል። እዚህ ላይ ደግሞ ዋጋቸውን ተቀበሉ የሚለው በምድር በሰው ልጆች ከንፈር ተመጦላቸው ምስጋና ቀርቦላቸው ዋጋቸውን እዚህ ተቀበሉ በሰማይ የሚጠብቃችው ዋጋ የለም ሲለን ነው።
        ዝና ሳንፈልገው ሊመጣ ይችላል። የጌታችን ደቀ መዛሙርት “ነገራቸው ወደ ዓለም ሁሉ ወጣ እስከ ምድርም ዳርቻ ደረሰ “ተብሎ እንደተነገረ መልካም ሥራው በጎረቤት በጓደኞቹ ሊታወቅ ይችላል ይህ በራሱ ስሕተት ሐጢያት ሊሆን አይችልም። ባለቤቱ በልቡ ካልተቀበለው ዝነኛ መሆን ሽቶ የማይሯሯጥ ለሰው ታይታ ብሎ የማይደክም ከሆነ ስህተት አይሆንበትም። ስህተቱ የእግዚአብሔርን መንግስት ረስቶ ለዝና ብቻ ከደከመና ከሮጠ ነው። ሰለዝና ብቻ መጨነቅ የክርስትና ጉዞ ዳርቻ እስከየት ድረስ እንደሆነ እንዳይረዳ ያደርገዋል። ዝነኛ መሆን የሚፈልግ ወጣት ዝነኛ መሆን ካልቻለ የሩጫው ፍጻሜ ይሆንና ሰዎቸ እንዳላወቁት በማሰብ ብቻ ሩጫዬን ጨርኛለሁ ይላል። ምናልባትም የጠበቀውን ዝና ካላገኘ ደግሞ ስለመንግሥተ ሰማያት ስለማያስብ ዝነኛ ካልሆንኩ ምንእሰራለሁ በሚል ቤተክርስቲያንን ጥሎ ይኮበልላል።
          አንድ የማውቀው ወጣት ትዝ ይለኛል።ቤተ ክርስቲያን በመጣበት ዓመት ስድስት ወር ሳይሆነው ሁሉንም መሆን ተመኘ ሰባኪ ሲመለከት ሰባኪ፣ ዘማሪ ሲያይ ዘማሪ፣ዲያቆን ሲያይ ዲያቆን፣ባህታዊያን ሲያይ ባህታዊ፣ ለመሆን ያልሞከረው የለም በየዕለቱ በየሳምንቱ ሃሳቡን ይቀያይራል።ካሴት ላወጣ ነው፣ ካህናት ማሰልጠኛ ገብቼ ኮርስ ወስጄ ጎበዝ ሰባኪ ልሆን ነው፣ ገዳም መግባት አስቤያለሁ፣ ይላል።እንዲህ ሁሉንም እየተመኘ ለአንድ ዓመት ቆየ።ከዚያ ሁሉም ስላልሆነለት ተበሳጭቶ ከቤተክርስቲያን ተለየ፡ ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከተለየም በኋላ ነጋዴ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ሯጭ የመሆን ሙከራ ያደርግ ስለነበር የሰፈር ጓደኞቹ መቀለጃ ሆነ።  ' ይህ ወጣት መጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ለክብር ለዝና ታዋቂ ለመሆን ቢሆንም ጥቂት አየቆየ ሲሄድ ቢበስል መልካም ነበር። ነገር ግን ነገሮችን ሳያገናዝብ በዚያው በመጣበት ሐሳብ እንደጸና ለዝናና ለክብር ብቻ እንደሮጠ ከቤተክርስቲያን ተለየ።
           ሌላ ወጣት ደግሞ አስታውሳለሁ። ወደ ቤተክርስቲያን የመጣው የአንድ ሰባኪ ስብከት ሰምቶ እንደ እርሱ ለመሆን ነው። እንደገባ አካባቢ በየጽዋ ማሕበሩ ካልሰበኩ ለማለት ሞከረ።የሚያውቀውንም የማያውቀውንም እየተናገረ ባልበሰለ ሕሊናው ለመስበክ ሞከረ። የኋላኋላ ግን ወደ ውስጥ እየዘለቀ ሲገባ በገዳማት ያሉ አባቶችን ሊቃውንትን መምህራንን ሲመለከት በራሱ አፈረ። ከዚህ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት በሚገባ ሳላጠና ሕይወቴ ሳይለወጥ አልሰብክም ብሎ መንፈሳዊ ሕይወቱን ብቻ ማስተካከል ቀጠለ፡፤ ለብዙ ዓመታት በንስሃ በፆም በጸሎት ሕይወቱን ፈተሸ። ለመንግሥተ ሰማያት የሚያስፈልገውም መንፈሳዊ ሆኖ መገኘት እንደሆነ ሰለተረዳ እጅግ መንፈሳዊ ሆነ። ኋላ ላይ የስብከት አገልግሎት ፀጋዬ አይደለም እኔ እግዚአብሔርን የማገለግለው አባቶችን በመርዳት ነው በሚል ከደሞዙ አስራት በማውጣት ጓደኞቹን በማስተባበር ሰዎች ሳያውቁበት በየገዳማቱ ያሉ አባቶችን መርዳት ቀጠለ። ይህ ወጣት የመንፈሳዊ ሕይወት ምንነትን ባይረዳ ኖሮ ስብከቱ አልሆን ሲለው ከክርስትናው ይለይ ነበር። መንፈሳዊነት ምን እንደሆነ ስላወቀ በሃይማኖት በምግባር ጸና።የጉዞው ፈጻሜ ለአገልግሎት መድረክ ላይ መውጣት ሳይሆን መንግስተ ሰማያት ለመግባት እስከ ሕይወት ፍጻሜ መጽናት መሆኑን አወቀ።
    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል"የእግዚአብሔር ስም በአንተ እንዳይነቅፍ ከፈለግህ ስለ ዝና አትጨነቅ ። በሌላ በኩል ሌሎች ስላንተ ክፉ እንዲያወሩም መንገድ አትስጣቸው በእነዚህ በሁለት ጉዳዮች ጠቢብ ሁን ።”ስለ ዝናው የሚጨነቅ ሕይወቱ በሁከት የተሞላ ይሆናል። ጸጥታ የልብ መረጋጋት ሰላም አይኖረውም። የገበያ ውጣ ውረድ እንደሚያስጨንቀው ነጋዴ በመታወቅና ባለመታወቅ መካከል ሆኖ ሲጨነቅ ሲጠበብ ይኖራል። ምን ያህል ሕዝብ አወቀኝ? ሰዎች ስለኔ ምን ይላሉ? በሚል ብቻ ሌትና ቀን እንቅልፍ ያጣል።ይህ ደግሞ ረጅሙን ጉዞውን ያስረሳዋል። ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይነጋገር ያደርገዋል።
                                                                     ይቆየን


ሐሙስ 17 ጁላይ 2014

ምሥጢረ ሥላሴ ክፍል ሁለት

እግዚአብሔር አብ

• ስለ ወይኑ ዛፍ ስናስብ ቀድሞ የሚታሰበን ሥሩ ነው፡፡  እውነተኛ ዛፍ ሥር አለው፡፡ ሥር የሌለው ዛፍ የለም፡፡ ካልሆነ ግን ቃል ወይም
ሐሳብ እንጂ እውነተኛ ዛፍ ሊሆን  ይችልም፡፡
• ለእያንዳንዱም እንደዚሁ አባት አለው፡፡አባት የሌለው በራሱ ያለና የሚኖር አስገኝ የሌለው “የሁሉ አባት” ግን ማነው? የሁሉ አባት እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡እግዚአብሔርንም አባት ለማለት አብ ብለን እንጠራዋለን፡፡እ ርሱም ከሦስቱ አካላት አንዱ ነው፡፡
ነገር ግን አባት ስንል ምን ማለታችን ነው?
1. የእግዚአብሔር ወልድ - የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ነው፡፡
• ጌታችን እውነተኛ የወይን ግንድ ነኝ ብሎናል፡፡ ዮሐ 15፡1፡፡ ነገር ግን የማን ልጅ ነው? “ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥
ኢየሱስ፦ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው።” ማቴ 22፡42፡፡
• ጌታችን እንደ ሰው ከሥጋ አባት ተወልዶ ቢሆን ስለ ሥጋ አባቱ ይነገረን ነበር፡፡
• ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌሎች እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንደሆነ ስለ ተለያዩ ምክንያቶች ያምናሉ፡፡
• የማይታይ የማይመረመረው እግዚአብሔር (አብ) የእግዚአብሔር ወልድ የኢየሱስ ክርስቶስ  አባት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስም በወይኑ ዛፍ ምሳሌ “ገበሬውም   አባቴ ነው”  እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች እግዚአብሔርን (አብ) “አባቴ” ብሎ
ጠርቶታል፡፡
• ቅዱስ ጳውሎስም   እግዚአብሔር (አብ) “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” ብሎ ጠርቶታል፡፡ ካል ቆሮ 1፡3፣ ካል ቆሮ 11፡31፣ኤፌ 1፡3፣ ኤፌ 3፡14፡፡
• ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር  አብ የተገኘ ነው፡፡ ጌታችን ራሱም “ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን ተወዋለሁ ወደ አብም  እሄዳለሁ።” ዮሐ 16፡28፡፡ ብሎናል፡፡
• በትንቢትም “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥አ ንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” ሚክ 5፡2 ተብሎ ተነግሮናል፡፡

• ጌታችን “ሕያው  አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል፡፡” ዮሐ 6፡57፡፡ ብሎናል፡፡
• ከክርስቶስ እኩል የእግዚአብሔር አብን አባትነት እጋራለሁ የሚል አይኖርም፡፡እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ    አባትነቱ በተፈጥሮ ሕግ እንደሚሆነው (በማግባትና በመውለድ) አይደለም፡፡
•እግዚአብሔር መንፈስ ነውና ስለርሱ የምንናገረውም በመንፈሳዊ መንገድ ነው፡፡
2.እግዚአብሔር የሁሉ አባት ነው
•እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ “ለሁላችንአ ንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?
የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?” ሚል 2፡10፡፡ ብሎናል፡፡
• ሊቀ ነቢያት ሙሴም እስራኤልን “ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ? የገዛህ
አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው።” ዘዳግ 32፡6፡፡ ብሎናል፡፡
• ነቢዩ ኢሳይያስም “አሁን ግን፥አቤቱ፥አንተ አባታችን ነህ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን።”ኢሳ 64፡8፡፡ ብሎናል፡፡
• ቅዱስ ጳውሎስም “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” ቀዳ ቆሮ 8፡6፡፡እንዲሁም “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።” የሐ ሥራ 17፡28፡፡ ብሎአል፡፡
3. እግዚአብሔር የሚያምኑበት አማንያን ሁሉ አባት ነው
• እግዚአብሔር ስለወደደንና ስለራራልን እኛም አምላክነቱንና አባትነቱን አምነን በጥምቀት በመወለዳችን አባታችን ይባላል፡፡ “በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።” ኤፌ 1፡5፡፡
• ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ነው ብለን ለምናምን ሁሉ እግዚአብሔር አባታችን ነው፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡” ዮሐ 1፡12፡፡
ማጠቃለያ
እግዚአብሔር አብ
1. የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድያ ልጁ ነው፡፡
2. ሁሉን ፈጥሯልና የፍጥረታት ሁሉ አባት ነው፡፡
3. በርሱ የሚያምኑ ሁሉ አባት ነው፡፡
4. የሕይወት ምንጭ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም የወጣው (የሠረጸው) ከእርሱ ነው፡፡ ዮሐ 15፡26፡፡

• በሐዲስ ኪዳን በእግዚአብሔር አብ ማመን ማለት በአንድ እግዚአብሔር ማመን ማለት ነው፡፡አባት የሚለው የሚምታታባቸው የእግዚአብሔርን አባትነት ከሥጋ አባትነት ጋር ከማገናኘት መቆጠብ ይገባቸዋል - አባትነቱ የሥጋ አባትነትን አያመለክትምና፡፡