2014 ጁላይ 12, ቅዳሜ

ክርስትናና ወጣትነት/ክፍል አንድ/
በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን
  ሰላሌ ሃገረ ስብከት እያለሁ ነዉ።አስታውሳለሁ።ወረዳ ላይ ለአገልግሎት ስወጣ የሚያጥመኝ የሚገርምኝም ነገር ነበር።የሰንበት /ቤት ወጣቶችን ሳስተምር ከመካከላቸው ሁል ጊዜ አንድ አዛውንት አያለሁ።ወጣ ካለ ቦታ ከገጠር ነው የሚመጡት። ብርቱ የሆነ መንፈሳዊ ስሜት አላቸው።በአካባቢያቸው ብዙ ጨሌ አቃጥለዋል።በዛ ያሉ ምዕመናንም ለንሰሓ አብቅተዋል።ለገጠሩ ሕብረተሰብ ጥሩ አርበኛ ናቸው።እኒህ አረጋዊ ጉባኤ ሲያበቃ ይጠራቀሙትን አንድ መድበል ጥያቄ ይዘው ይመጣሉ።ከዚያ በቃ መጽሓፍ ቅዱስ እየገለጡ መጠየቅ ነው።መናፍቃንን አጥብቀው ስለሚቃወሙ ለእነርሱ የሚሆን መልስ በጉንጫቸው አለ።                
           ታድያ ብዙ ጊዜ የሚናገሩት ነገር ነበር።እንደው እድሜን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም እንጂ ምነው በተቻለና በመለስኩት፣  በእኛ ጊዜ የሃይማኖት ትምህርት እንዲህ ስላልተስፋፋ ባተሌ ሆነን ነው የኖርነው ይላሉ። እናንተ ታድላችኋል ዕድሜያችሁን እየተጠቀማችሁበት ነው በማለት በቁጭት ይናገራሉ። መዝሙር ሲዘመር ስብከት ሲሰበክ፣ ሰንበት /ቤት ድራማ ሲሰራ በቃ እርሳቸው ከራሳቸው ጋር ይሟገታሉ። እድሜ ከንቱ ሳላውቀው ሄደና በቃ ወጣትነቴ አመለጠኝ ማለት የዘወትር ተግባራቸው ነው።
            አንድ ቀን መከርኳቸው መንፈሳዊ ቅናት መቅናታቸው መልካም ቢሆንም ለቀቢፀ ተስፋ እንዳይዳርጋቸው ይተዉ። የእርስዎ የጥሪ ዕድሜ ይሄ ከሆነ ስልሳኛ አመትዎንም እንደ ሃያና ሰላሳ ይቆጥርልዎታል ይልቅስ ባልዎት ዕድሜ እየተጠቀሙ ይበርቱ ብዪ አጽናናኋቸው ።በወጣቱ እንቅስቃሴ የሚገረሙ ምዕመናን ይህን ይላሉ ።ምነዉ ዳግመኛ በተፈጠርኩ ፣ምነው ወጣትነቴን በድጋሚ ባገኘሁት ይላሉ።ግን አይሆንም ዕድሜ ከነጎደ ነጎደ ነው።ከመፀፀት አንዷን ዲናር /መንግሥተ ሰማያትን/ ዋጋቸው ሆና ለመቀበል በገቡበት ሰአት ገብተው ታማኝ ሆነው ድራሻቸውን ቢወጡ መልካም ነው።የሦስተኛውም የስድስተኛውም የዘጠነኛውም ፣ሰአት ዋጋ አንድ ዲናር ነው።
            ዕድሜ ሳይሰሩበት ያለፈባቸው እንዲህ እንዲጽናኑ እየመከርን ወጣትነት በእጃችን ያለ ግን ብዙ ይጠበቅብናል።ዛሬን እንደ ቀልድ ባተሌ ሆነን ካሳለፍነው ነገ መጸጸት እንድሚመጣ መዘንጋት የለብንም። ወጣትነታችን ጥሎን ሳይሄድ እያንዳንዱን ደቂቃ ሰከንድ እንዳይባክን አድርገን ማሳለፍ ይጠበቅብናል።ዕድሜ በላያችን ሳይሮጥ እኛ በእድሜ እንሩጥ።ጊዜን እየገደልነው ሳይሆን እየተጠቀምንበት እንዲያልፍ እናድርግ።ለሌላው ንብረታችን ከምንሳሳው በላይ ለዕድሜ እንሳሳ።መክሊቱን ቀብሮ ያለ ትርፍ እንደተገኘው ሰነፍ ባሪያ የተሰጠንን ጊዜ ሳናተርፍበት ባለቤቱ እንዳይመጣብን እንጠንቀቅ።
            ለመጸለይ ዓይኔን ፣ለመስገድ ወገቤን ፣ለመፆም አቅሜን የማንልበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።ከልብ ከተነሳን በዚህ ዕድሜ በፈጣሪ እርዳታ ብዙ መስራት እንችላለን።ለአገልግሎት ከአንዱ ስፍራ ወደ አንዱ ብንሮጥ፣ገዳማቱን በየሥፍራው ዞረን ብንሳለም ፣አበውን ለመርዳት ገንዘብ ብናወጣ ፣ብንረዳ ፣መንፈሳዊ ማህበር ብንመሰርት ሁሉም ይቻላል።ጉልበትን ገንዘብን፣እውቀትን፣ሁሉንም በስራ ለማዋል የሚመቸው በዚህ ዕድሜ ነው።
           የመናፍቃንን ተንኮል ለመከላከል ዘመኑን ዋጅተን መልስ ማዘጋጀት የምንችልበት እድሜ ወጣትነት ነው።በየዋህነት የኮበለለውን  ምዕመን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ በአፍ በመጽሐፍ የምንልበት ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ ሌትና ቀን የምንደክምበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።በዚህ ዕድሜ ቅዱስ ዮሐንስ ነገረ መለኮትን አርቅቆ አምጥቆ እንደጻፈ / ዮሐ 21-24 /አትናቴዎስ የሃይማኖት ጸሎትን ከሦስት መቶ አስራ ስምንት ሊቃውንት ጋር በመሆን እንዳረቀቀ አንርሳ።
           ሰማዕትነት ቢመጣ አንገትን ለሰይፍ ለስለት ፣ሰውነትን ለሞት ለመስጠት የሚታገሱበት ዕድሜ ወጣትነት ነው።ስለቤተክርስቲያን ሕይወትን እንኳን ዋጋ አድርጎ ለመስጠት ይህ ዕድሜ ይመቻል።ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የአይሁድን ቁጣ ሳይፈራ እውነትን መስክሮ በሰማዕትነት ያረፈው በእዚህ እድሜ መሆኑንም አንዘንጋው።ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዐላውያን ነገሥታት ፊት ስለአምላኩ መስክሮ የገጠመውን መከራ ሁሉ በጽናት የተቀበለው ገና በሃያ ሦስት ዓመቱ ነው።ከቅዱሳት አንስት ቅድስት አርሴማን የመሳሰሉ እናቶች መከራን ስለ ሃይማኖታቸው የተቀበሉት በዚህ እድሜ ነው።
           ከዚህ ሁሉ አንጻር በወጣትነት የዕድሜ ክልል ያለን ቤተ ክርስቲያንን በጽናት በትጋት ማገልገል ይጠበቅብናል።ዕድሜያችን ለመንፈሳዊነት የሚመች እንደመሆኑ እንጠቀምበት።በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪያችንን ማሰብ እንዳለብን አንዘንጋ።/መጽ መክ 12-1/ ውድ የሆነዉን የዕድሜ ክልላችንን ለእግዚአብሔር አንንፈገው።ይልቁንም ከእጁ የተቀበልነዉን እድሜ ፣ጤና ….መልሰን ለፈጣሪ እንስጠው።ጤናችን ፣ጉልበታችን ፣ገንዘባችን ሁሉ የእርሱ ነው።የእኛ የሆነ አንዳች ነገር የለንም።ሌላው ቀርቶ እኛም እራሳችን የእርሱ ነን።ይህንን ሳንረሳ ሁል ጊዜ ለፈጣሪ ታማኝ እንሁን።
          ወደፊት በዚህ ዓምድ ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን እንዴት መመላለስ እንዳለበት ፣መንፈሳዊ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለበት በሰፊው እንመለከታለን ።የሚገጥሙትንም ፈተናዎች በጊዜዉና በሰዓቱ እንዳስሳለን።ለአሁኑ ይቆየን።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ