2014 ጁላይ 12, ቅዳሜ

ውዳሴ አምላክ ዘ እሑድ
የንስሐ ሥርዓት
የመመኘቴ ጸሎት ጌታዬ መድሐኒቴ ኢየሱስ ሆይ እንግዲህ በእኒህ ሁሉ አማላጅነት ወደእኔ ና አትዘግይብኝ ነፍሴ እና ልቤ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጥነህ ና በሉት አፌ ኢየሱስ ክርስቶስን ና በለው  የጻድቅነት ጸሐይ ሆይ የነፍሴን ጨለማ አርቅልኝ ሰማያዊ እሳት ሆይ በዓለማዊ ፍቅር ብርድ ለታሰረብኝ ልቤ ያንተን ፍቅር ሙቀት ስጥልኝ ጌታዬ ሆይ በወንጌል ለመቶ አለቃ ወደ ቤትህ እመጣለሁ ልጅህንም እፈውስልሀለሁ እንዳልከው ለነፍሴ ወዳንቺ እመጣለሁ እፈውስሻለሁ በልልኝ ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ እንዳልናገር አፌን ፈውስኝ ክፉ እንዳለይ አይኔን ፈውስልኝ ክፉ እንዳይሰሩ ነፍሴንና ስጋዬን ፈውስልኝ ጌታዬ ሆይ የእኔን የሎሌህን ክፋት ልትተው ና አትዘግይብኝ ቅዱስ መልአኬ ነፍሴን እጅግ የምትወድ ጠባቂዬ ሆይ ስለ እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይህንን ኑዛዜ በቀኖና በትህትና በሐዘን በፍቅር እንዳደርገው አግዘኝ
ስለኑዛዜ ምክር እንዲህ እያለ የሀዘን ጸሎት እያደረገ በትህትና በልብ ይጸጸት
ዘእሑድ ውዳሴ አምላክ
አቤቱ የጠራ የልቦናን ለቅሶ ስጠኝ ጌታዬ ሆይ በእኔ የጸኑ እሾህ እና አሜኬላን ክዳት ተንኮልንም አጥፋልኝ ዘወትር የሚያቃጥል ልቅሶን ስጠኝ አቤቱ የሰይጣን ገንዘብ የሚሆን የኃጢአትን ጣዕም ስር ከእኔ ነቅሎ የሚጥል ልቅሶን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ከኃጢአት የሚመለሱ ሰዎችን ልቅሶ ስጠኝ አቤቱ የቅዱሳንን ልቅሶ ስጠኝ፡፡ አቤቱ በኃጢአት ሳለ እንዳይሞት ስለራሱ ያለቀሰ የዳዊትን ዕንባ ስጠኝ ፡፡
ጌታዬ ሆይ እንደኔ የበደለ የለምና እኔም እንደወደቅሁት አወዳደቅ የወደቀ የለምና እኔ እንደተፈተንኩት የተፈተነ የለምና፡፡ የሠራትም ኃጢአት አንዲት ብቻ አይደለችምና በኃጢአቴ የሌላውን ጽድቅ አጠፋሁ እንጂ፡፡
ጌታዬ ሆይ እኔን ሳላውቅ የፈጠርኸኝ አንተ ነህ ፡፡አንተ ጌታዬ የከበርህ መምህር ኃያል ገናና ነህ እኔ ባርያህ ግን የተናቅሁ ጎስላ ደካማ ነኝ አፌ የሚሸት ነው አንደበቴም ዲዳ ነው፡፡ እኔም ኃጥእ ነኝ፡፡ ደካማ ነኝ ልቤም የረከሰ ነው፡፡ በቸርነትህ ተጠግቼ እጠራሀለሁ የጻድቁንና የኃጥኡን ጸሎት የክፉውን የምትሰማ አንተ ነህና ያለ አንተም ቸር የለምና እንደ አንተ ያለ ይቅር ባይ የለምና፡፡ 
ጌታዬ ሆይ የነጻች የእጅህ ሥራ ነኝና ስለ ኃጢአቴ ቸል አትበለገኝ አቤቱ ሥጋዬን አንጻው ሕፀፄን አውቄ ከመጠኔ እንዳልወጣ አቤቱ ጠላት ድል እንዳይነሳኝ ኃይልን ስጠኝ በክብርት ጥምቀትህ የተሠራች ቤት ሥጋዬን እንዳያፈርሳት በከፋች ኃጢአት እንዳያሳድፋኝ ስለ ኃጢአቴ ሥርየት ወደ አንተ እማፀናለሁ፡፡ አቤቱ ነፍሴ እንዳትጎዳ አደራህን ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለ ጉስልናዬና ስለ ጉዳቴ እማፀናለሁ ስለ ኃዘኔና ስለ መከራዬ በአንተ እማፀናለሁ ስለ መልኬ ጥፋትና ስለበደሌም በአንተ እማፀናለሁ፡፡ ብሩህ ሁኜ ሁሉን እንዳላይ የጠቆርሁ ኃጥእ ነኝና ላልተመለሱ ፍርድህንና ሞትን ማሰብ ስጠኝ አቤቱ በደሌንና ነውሬን የሚያጥብ ዕንባን ስጠኝ አቤቱ፡፡አቤቱ አንተን የሚያገለግል ዕንባን ስጠኝ አቤቱ ልዩ እንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ቀጡ ዕንባን ስጠኝ፡፡አቤቱ ኀዘኔን የሚያርቅልኝንና የፊቴን ጥቁረት የሚያርቅልኝ እንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ከዓይኔ ፈሶ የአካሌን እድፍ የሚያጥብልኝ ዕንባን ስጠኝ፡፡  አቤቱ አንተን ደስ የሚያሰኝ ደስ ብሎህ የምትቀበለው ዕንባን ስጠኝ፡፡
የተነሳሕያንን ዕንባን የምትቀበል ሆይ ወንድማቸውን ከመቃብር እስክታነሣላቸው ድረስ ሳያርጡ እንዳፈሰሱት እንደ አልአዛር እህቶች ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡አንተ የተቀበልከው ጽኑ ልቅሶን እንደ አለቀሰ እንደ ጴጥሮስ ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡
ከንጹሐን እግሮችህ ላይ ዕንባዋን አፍስሳ በራሷ ፀጉር  እንደ አደፈችው እንደ ሴሰኛዪቱ ሴት ያለ ልቅሶን ስጠኝ፡፡ልቅሶዋም ስለ ንስሐዋና ስለ ሕይወትዋ ሆነ፡፡
ልጅዋን እንዳነሣህላት እንደ ጎስላይቱ ድኻ ልቅሶ ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡አልጋዬን በዕንባዬ አርሰዋለሁ ምንጣፌን በዕንባዬ አጥበዋለሁ ብሎ በስድስተኛው መዝሙር  እንደ ተናገራት እንደ ዳዊት ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡
አቤቱ እንደ አባቶቼ መምህራን ያለ ዕንባን ስጠኝ፡፡ እንደ ተነሳሕያን ኃጥአን ያለ ዕንባን ስጠኝ አቤቱ እንደ ባሕር በምትፈስ ዕንባ እጠበኝ፡፡ አቤቱ ጌታ ሆይ የተዘጋ ደጅህን ክፈትልኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ የማያርጥ የዕንባን ምንጭ ክፈትልኝ፡፡ አቤቱ የማያርጡ የዕንባዎች ጎርፍን አፍስልኝ ፡፡ስለበደሌና ስለኃጢአቴ ብዛት ስለ ነፍሴም ጉዳት የንግድ ገንዘብ ስለሚሆን ስለራሴም ጥፋት አቤቱ ይቅር በለኝ፡፡
ጌታዬ ሆይ ነፍሴን ከሥጋዬ እስክትለይ ርዳት የተበላሸች የወይን ቦታ ስለ መልካም ፍሬ ፈንታም ርኩስ ፈቃዴና ኃጢአቴ የሰለጠኑበትን አርማት ኮትኩታት፡፡
ጌታዬ ሆይ ወደ መመቸቴ ፈቃድ አታግባኝ፡፡ ፍርድህንም ፈርቼ ነፍሴን ከፊትህ ጥያታለሁ፡፡ አቤቱ ከይቅርታህ ለምመጸወት ድኻ እዘንልኝ ከርኅራኄህ ትሩፋት የምለምን ችግረኛህንም አታሳፍረኝ፡፡ በበደሌና በኃጢአቴ መታደስ  እኔ ወራዳ ድኻ ነኝና በከሃኒነትህ ከኃጢአት እድፍ አንጻኝ ስምህን ለሚወዱ ለባሮችህ ባዘጋጀኸው በንስሐ ዕንባ እጠበኝ ፡፡
አቤቱ ኃፍረቴንና ኃሣሬን ሠውራት፡፡ በፍጥረቱ በምትፈርድበት ጊዜ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ስማኝ ፈጣሪዬ ሆይ ፊትህን ከልመናዬ አትመልስ፡፡ልቅሶዬን ተቀበል ዕንባዬንም አታሳፍር አኔ ጥገኛህ ነኝና ጌታዬ ሆይ ስለ ኃ ጢአቴ ብዛት እገዛልኻለሁ፡፡
ጌታዬ ሆይ እስከዘመኔ ፍጻሜ ከቡር ስምህን አመሰግናለሁ ኪሩቤል ሱራፌልም የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ አንተን ያመሰግናሉ ለዘላለሙ አሜን በእውነት ይደረግልገኝ፡፡

መዝሙረ ዳዊት 120
1 ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?
2 ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
3 እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም የሚጠብቅህም አይተኛም።
4 እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።
5 እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።
6 ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።
7 እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።
8 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ