በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን
መንፈሳዊ ዕውቀት
ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ሲኖሩ
ገንዘብ ሊያደርጉ ከሚገባቸው ነገር አንዱና ዋነኛው መንፈሳዊ ዕውቀት ነው።ስለዚህ በሃይማኖት ስንኖር መንፈሳዊ ዕውቀት ገንዘብ
ማድረግ ይገባናል። ከዚህ ቀጥለን በክርስትና ሕይወት ስንኖር የመንፈሳዊ ዕውቀት ጠቀሜታ ምን እንደሆነ በተራ
እንመለከታለን።
1.ስለ ሃይማኖት
የምናውቅበት ነው።
ሃይማኖት ሀልወተ
እግዚአብሔርን፣ነገረ ቅዱሳንን፣ሥርዓተ ቤት ክርስቲያንን፣....የምንረዳባት የነፍስ መንገድ ናት፡፡ይህች መንገድ በእምነት
ለተከተላት የነፍስን እረፍት ታሰጣለች /ኤር.6÷16/፡፡ሃይማኖት ሁለትና ሦስት ሆና መከፈል ሳይኖርባት በቅዱሳን በኩል
የተሰጠችን አንዲት መንገድ ናት፡፡የያዕቆብ ወንድም ሐዋርያው ይሁዳ“ወአስተበቍዐክሙ ከመ ትትቀነይዋ ለእንተ ተውህበት ለቅዱሳን
ሃይማኖት”ለቅዱሳን/ለሐዋርያት/የተሰጠችውን ሃይማኖት ትይዝዋት ዘንድ እማልዳችኋለሁ”ይላል/ይሁዳ1-3/።ይህች ለቅዱሳን የተሰጠች
ሃይማኖት አንዲት እንደሆነች ቅዱስ ጳዉሎስም እንዲህ በማለት ይመሰክራል“አሐዱ እግዚአብሔር።ወአሐቲ ሃይማኖት።ወአሐቲ
ጥምቀት።እግዚአብሔር አንድ ነው።ሃይማኖትም አንዲት ናት።ጥምቀትም አንዲት ናት።”/ኤፌ 4-5/ ።ታዲያ ለአባቶቻችን
ሰለተሰጠች አንዲት ሃይማኖት ምንነት በትክክል ለመረዳት አንድ ዐቢይ ነገር ያስፈልጋል።እርሱም መንፈሳዊ ዕውቀት ነው።መንፈሳዊ
ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ ሰው ሃይማኖቱን በትክክል ያውቃታል፡፡ምስጢራት ሲፈጸም በውስጧ ሲመላለስ በልምድ ሳይሆን በዕውቀት
ያደርገዋል፡፡ከእርሱ አልፎ ሌሎችም ስለ ሃይማኖታቸው በትክክል እንዲረዱ ያስተምራል ይመክራል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ“ሠናየ
ገድለ ተጋደልኩ።በድርየኒ ፈጸምኩ።ወሃይማኖትየኒ ዐቀብኩ።በጎ ገድልን ተጋደልኩ።ቅድድሜንም ጨረስኩ።ሃይማኖቴም
ጠበቅሁ።”/2ጢሞ5-4/ይለናል፡፡በተጋድሎ ጸንቶ መቆየቱን፣ሩጫውን መፈጸሙን ሲገልጽ አብሮ ያስቀመጠው ትልቅ ነገር ሃይማኖቱንም
መጠበቁን ነው።ገድል ያለ ሃይማኖት አይሆንም።መንፈሳዊ ሩጫም ያለ ሃይማኖት ከንቱ ነው።ለዚህ ነው ሐዋርያው በዘመኑ ፍጻሜ
በሃይማኖት መጽናቱን የሚመሰክርልን።እናንተም በሃይማኖት ጸንታችሁ ኑሩ ሲለን ነው።አባቶቻችን እሳት ስዕለቱን ሳይፈሩ
በሰማዕትነት ያለፉት፣ በድንጋይ ተቅጥቀው በመጋዝ ተሰንጥቀው ያለፉት፣ይህን እውነታ ስላወቁ እና ስለተረዱ
ነው፡፡የአባቶቻችን ሐዋርያት፣ቀጥሎም ሊቃውንት፣የእነ አትናቴዎስ፣ዲዮስቆሮስ፣ቄርሎስ፣ሃይማኖትን ከጠበቅን እኛም እነርሱ ከገቡበት
መንግሥተ ሰማያት እንገባለን።እነርሱ ከደረሱበት ክብር እንደርሳለን።
ወጣቱ ከዚህ አንጻር
በሃይማኖት እንዲጸና በሰንበት ትምህርት ቤት የጀመረውን አገልግሎት ከዳር እንዲያደርስ መንፈሳዊ ዕውቀት ያስፈልጋል።በዘመናችን
ወጣቱ ብዙ ተጋድሎ ይጠብቀዋል።ከሥጋ ፈቃዱ ታግሎ ራሱን ከማሸነፍ ጀምሮ ሌሎች ብዙ የተጋድሎ መንገዶች ከፊቱ አሉ።ይህንን ድል
ለመወጣት መንፈሳዊ ዕዉቀትን ገንዘብ አድርጎ መገኘት ግድ ነው።ሃይማኖትህ ርትዕት/ቀጥ ያለች /እንደሆነች ከወላጆችህ
ሰምተህ ይሆናል።አባቶች በተለያየ አጋጣሚ ሲመሰክሩላት ሰምተህ ይሆናል።መልካም አድርገሃል።ከዚህ ጋር ግን ቀጥተኛ መሆኗን
ለመረዳት ምን አደረግህ።በሰዎች ላይ ተደግፈሃል?ወይስ እራስህን ችለህ ስለ ሃይማኖትህ ትመሰክራለህ?ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት
እዉነተኛ መሆኗን የምትናገረው ተምረህ ተረድተህ ነው ወይስ በልምድ እና በስሜት ሆነህ?ይህን ጥያቄ ለራስህ ጠይቅና መልሱን
ለማግኘት ሞክር።
2.ከመናፍቃን
የምንጠበቅበት ነው።
ስለሃይማኖታችን በሚገባ
ስናውቅ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩ የኢአማንያን እና የመናፍቃን ጥያቄ አያሰጋንም፡፡በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለሚነሳ ጥያቄ አጥጋቢ
መልስ መስጠት እንችላለን፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ‹‹በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት
የተዘጋጃችሁ ሁኑ›› /1ጴጥ.3÷15/እንዳለው ክርስቲያን ስለሚያምነው እምነት መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆን
አለበት።መናፍቃን፣ኢአማንያን በአፍ በመጣፍ ሲመጡበት እንዳመጣጣቸው መመለስ መቻል አለበት።ለዚህም መፍትሔው አውቆ ተረድቶ
መገኛት ነው።ቅዱስ እስጢፋኖስ በወጣትነት ዕድሜው አይሁድን ፊት ለፊት የገሠጸው ስለ ክርስትናውም በድፍረት የመሰከረው
ስለ ሃይማኖት የነበረው ዕውቀት ምሉዕ ስለነበረ ነው።/ሐዋ 7/ጢሞቴዎስም ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዶሳት መጻሕፍትን በመማሩ /2ጢሞ
3-15/ቅዱስ ጳውሎስንም ተከትሎ ስለሃይማኖቱ በሚገባ በማጥናቱ በወጣትነት ዕድሜው የቤተ ክርስቲያን አደራ ለመወጣት
በቅቷል።አትናቴዎስ የመንፈስ አባቱን እለ እስክንድሮስን ተከትሎ በተገኘበት የኒቂያ ጉባኤ መናፍቁ አሪዎስን መልስ ያሳጣው፣ለተሰነዘረው
የክህደት ሃሳብ አጥጋቢ መልስ የሰጠው በመንፈሳዊ እውቀት የበለጸገ ስለነበረ ነው።
በእኛም ዘመን
በነገረ መለኮት ዕውቀታቸው የሚመሰከርላቸው።ሃይማኖታቸውን በትክክል የሚመሰክሩወጣቶች ያስፈልጋሉ።መናፍቅ ሲያገኛቸው ራሳቸውን
ችለው መልስ የሚሰጡ ወጣቶች ያስፈልጉናል።ስለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት፣ስለ እመቤታች ቅድስት
ድንግል ማርያም ክብር አማላጅነት፣ስለቅዱሳን መላእክት፣ቅዱሳን አባቶች፣የማማለድ ሥልጣን በትክክል የሚመሰክሩ ወጣቶች
ያስፈልጉናል።የመናፍቃን ጉዳይ ሲነሳ የሚጨንቃቸው፣በሰንበት ትምህርት ቤት ሲያገለግሉ ታይተው ስለ
ሃይማኖታቸው ሲጠየቁ መልስ መስጠት የሚከብዳቸው ወጣቶች ለመንፈሳዊ ዕውቀት ቦታ መስጠት አለባቸው።
3.ስለቤተ ክርስቲያን
ሥርዓት የምንማርበት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ
‹‹ወንድሞች ሆይ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም እናዛችኋለን”ይላል /2ተሰ.3÷6/፡፡ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሥርዓቷን እንዲያከብሩላት ታዝዛለች፡፡ከሥርዓት የሚወጣውን
ትመክራለች፡፡ካልተመለሰ ትለያለች፡፡የፆም ሥርዓት፣የጸሎት ሥርዓት፣ … አላት፡፡ይህንን የፆም ሥርዓቷን ከአበው ተቀብላ ለልጆቿ
ሳይሸራረፍ ሳይበጣጠስ እንዲተላለፍ ትሻለች። ምክንያቱም ሥርዓቷ ሰማያዊ ነውና ነው/ሐዋ.7÷53/፡፡የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት
ለመጠበቅ ደግሞ ከሁሉ በፊት ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መማር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ቅዳሴውን ለማክበር፣በቤተ
መቅደስ የሚፈጸመውን የጸሎት ሥርዓት ለመፈጸም፣አፅዋማትን በሚገባ ለመፆም፣በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
ላይ ጠንከር ያለ መንፈሳዊ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡በዘመናችን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚታዩ
ችግሮች የሚፈጠሩት የተሐድሶ መናፍቃን አንዳንዶችን ለማታለል የሚሞክሩት የዕውቀት ማነስ ችግር ስላለ ነው፡፡ምእመኑ ስለ
ሥርዓቱን በሚገባ ቢያጠና መናፍቃኑ በቀላሉ አያስቱትም፡፡የአበውን ሥርዓት ‹‹ድሪቶ›› እያሉ ሲዘባበቱበት በጫማ ቤተ መቅደስ
እንዲገባ ሲያስተምሩት በዝምታ አያልፍም ነበር፡፡
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት
ዙሪያ ምን ያህል ተምረሃል?በቤተ መቅደስ የሚፈጸመውን የጸሎት ሥርዓት ቅዳሴውን፣ ሰዓታቱን፣ማኅሌቱን ለማወቅ ለመረዳት ምን
ያህል ጥረት ታደርጋለህ?የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ዓለም የሚለያትን ይህን የሃይማኖት ሥርዓት ለመረዳት ምን ያህል
ሞክረሃል?የምትፈጽመው እያንዳንዱ ምስጢር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ለመረዳት አባቶችን ለመጠየቅ ሞክረሃል?ወይስ የምትመላለሰው
በልምድ ነው?ለእነዚህ ጥይቄዎች ለራስህ መልስ ስጥ፡፡ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያለህ መንፈሳዊ ዕውቀት አነስተኛ ከሆነ
ለመማር ለማወቅ ለመረዳት ሞክር፡፡ለእናት ቤተ ክርስቲያንህ ባዕድ እንዳትሆን፣በቤትህ ለሚፈጸም ሥርዓት እንግዳ እንዳትሆን
ራስህን አዘጋጅ፡፡ውዳሴ ማርያም መድገም፣ቅዳሴ ማስቀደስ፣ማኅሌቱ ላይ መገኘት ዳገት የሆነባቸው፣በስንፍናቸው ምክንያት ቤተ
ክርስቲያንን በሚገባ ያላወቁት አንዳንድ ወጣቶች እንደሳቱ አስታውስ፡፡ ለተሐድሶ መናፍቃን መጠቀሚያ የሆኑ ወጣቶች አብዛኛዎቹ
የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ላይ ደካማ ጎን የነበራቸው ናቸው፡፡ለማወቅ፣ለመረዳት፣ጊዜ ሳይሰጡ በመቅረታቸው እንደሚገባ ሳያውቁት
ቀሩና ለስሕተት ተዳረጉ፡፡አንተ ግን ዶግማዋን ብቻ ሳይሆን ሥርዓቷን በሚገባ አጥናላት፡፡ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አድናቂ ብቻ
ሳይሆን ተጠቃሚም ለመሆን የተቻለህን ሁሉ አድርግ፡፡
5.ከስሕተት
የምንጠበቅበት ነው።
ስለ አግዚአብሔር ሕግ
የማያውቅ ምእመን በጨለማ ያለ ባትሪ ብርሃን እንደሚጓዝ መንገደኛ ነው፡፡በጨለማ የሚጓዝ መንገደኛ እንቅፋት እንደሚያገኘው፣ገደል
ወድቆ ውኃ ጠልቆ ሊጎዳ እንደሚችል ይህም ለማይሆን ስሕተት ይዳረጋል፡፡ሰይጣን በተለያየ ዓይነት ኃጢአት እንደፈቀደ
ያሰናክለዋል፣ያስተዋል፡፡ከግራኝ አህመድ ወረራ በኋላ በሀገራችን በደረሰው ጥፋት ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሊቃውንትን አጥታ
ቆይታለች፣ መጻሕፍት ተቃጥለውባት ለችግር ተዳርጋ ቆይታለች፡፡በዚህ ምክንያት ይመስላል ሕዝቡ ሃይማኖቱን በልምድ ብቻ
እንዲያውቀው ሆኖ የሰነበተው፡፡
በገጠሩ ያሉ ምእመናን
ጨሌና ጣዖት አምልኮን ከሃይማኖት ጋር ሲያገናኙ፣በከተማ የሚገኙ ምእመናንም አጽዋማትን ሸራርፈው በመፆም ፍልሰታ ረቡዕ እና
ዐርብ ይበቃሉ ሌላው የእኛ አይደለም ሲሉ፣የምንሰማው ከዕውቀት ማነስ ነው፡፡በተክሊል የሚፈጸም ጋብቻ ቀርቶ የመንግስታዊ ተቋማት
ጋብቻ በአብዛኛው ቦታውን ይዞ የምናየው በዕውቀት ማነስ ነው፡፡
በወጣትነትህ
ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብህ ትልቅ እድል ነው፡፡ይህ ዕድሜ ለማንበብ፣ለመጻፍ፣በጉባኤ ለመገኘት የምትችልበት ጥሩ እድሜ
ነው።ታዲያ በዚህ ምን ያህል ተጠቅመሃል?ጠይቀህ በመረዳት ፈንታ በስማ ባለው የመጣ ነገር ይዘህ የምትጓዝ ከሆነ ትልቅ
ስንፍና ነው፡፡ይህኛው ፆም የቄስ ነው ከማለት ቀርበህ ብትጠይቅ መልስ ታገኛለህ፡፡ዓሣ ፆም አይደለም ይባላል ብለህ የመጣ
ትምህርት ይዘህ ከመጓዝ አባቶችህን ብትጠይቅ መልስ ታገኛለህ።ቅዱስ ጳዉሎስ እንዲህ በማለት ልጁ ጢሞቴዎስን ይመክራል።“ስለዚህ
ወንድሞችን ብታሳስብ በእምነትና በተከተልኸዉ በመልካም ትምህርት ቃል የምትመግብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ
ትሆናለህ።ነገር ግን ለዚህ ዓለም ከሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ።”/ 1 ጢሞ 4-7/።
ይቆየን
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ